ኖርዌይ ከ28 ዓመት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ ለመመለስ ጣልያንን ትገጥማለች

You are currently viewing ኖርዌይ ከ28 ዓመት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ ለመመለስ ጣልያንን ትገጥማለች

AMN – ህዳር 07/2018 ዓ/ም

የአውሮፓ ሀገራት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይከናወናሉ።

በምድብ ዘጠኝ ቀዳሚውን ሁለት ደረጃ የያዙት ኖርዌይ እና ጣልያን በሳን ሲሮ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ለመጨረሻ ጊዜ በ1998 የፈረንሳይ የዓለም ዋንጫ ላይ የተሳተፈችው ኖርዌይ ከ28 ዓመት በኋላ ወደ መድረኩ ለመመለስ የተሻለ እድል አላት።

አስደናቂ ጉዞ ያደረገችው ኖርዌይ ሰባቱንም የምድብ ጨዋታዎች አሸንፋለች።

ጣልያን በአንፃሩ በመጀመሪያው ዙር በኖርዌይ ከተሸነፈችው ውጪ ስድስት ጨዋታ ማሸነፍ ችላለች።

ሁለቱ ሀገራት በሦስት ነጥብ ብቻ ቢለያዩም በመሃላቸው የ17 ግብ ክፍያ ልዩነት አለ።

በዚህ ምክንያት ጣልያን የኖርዌይን ቦታ ተረክባ በቀጥታ ለማለፍ ዛሬ ምሽት 4:45 ላይ የሚደረገውን ጨዋታ 9ለ0 ማሸነፍ አለባት።

በመጀመሪያው ዙር በኖርዌይ 3ለ0 የተሸነፈችው ጣልያን ይህን የማድረግ አቅም ይኖራታል ተብሎ አይጠበቀም።

በመጨረሻዎቹ ሁለት የዓለም ዋንጫ ያልተሳተፈችው የአራት ጊዜ የዋንጫ ባለቤቷ ጣልያን ለሦስተኛ ጊዜ ከመድረኩ ላለመራቅ በጥሎ ማለፍ ዙር እድሏን ትሞክራለች።

በሌሎች የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ፖርቹጋል አርሜኒያን ታስተናግዳለች።

ከቀናት በፊት በአየርላንድ 2ለ0 የተሸነፈችው ፖርቹጋል የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ቀጥታ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ያደርጋታል።

በአየርላንድ ሲሸነፉ ቀይ ካርድ የተመለከተው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ዛሬ 11 ሰዓት በሚጀምረው ጨዋታ አይሳተፍም።

በዚሁ ምድብ ሀንጋሪ ከ አየርላንድ በተመሳሳይ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

በምድብ አራት ማለፏን ያረጋገጠችው ፈረንሳይ ከሜዳዋ ውጪ አዘርባይጃን ምሽት 2 ሰዓት ላይ ትገጥማለች።

በምድብ 12 የምትገኘው ሌላኛዋ ሀላፊ ሀገር እንግሊዝ ምሽት 2 ሰዓት ከሜዳዋ ውጪ ከአልባንያ ጋር ትጫወታለች።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review