በየዓመቱ በሚከበረው ዓለም አቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ 4 ሺህ 375 ሁነቶችን በአንድ ዓመት ውስጥ በማዘጋጀት ብራዚልን በልጣ 1ኛ ሆናለች።
Global Entrepreneurship Week (GEW) የተባለው ተቋም ሀገራት በአንድ ዓመት ውስጥ ከሥራ ፈጠራ ጋር ያካሄዷቸውን ሁነቶች መዝግቦ ደረጃ በመስጠት ይታወቃል። ዛሬ ተቋሙ ይፋ ባደረገው ሰንጠረዥ መሠረት ሀገራችን በብራዚል ስትመራ ቆይታ ቀዳሚ ሆናለች።
ከህዳር 8 እስከ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በመላው ዓለም የሚከወነው የዘንድሮው ዓለምአቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት ‹በጋራ እንገንባ / Together We Build!› በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል፡፡ ሁነቱ በሀገራችን በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ በኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት እና በግሎባል ኢንተርፕረነርሺፕ ዊክ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ በጋራ ይከበራል።
ሳምንቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንተርፕረነሮች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩበት፣ አዲስ ሥራ የሚጀምሩበት፣ ምጣኔ ሀብታዊ እድገትን በተመለከተ ኢንተርፕርነሮች በጋራ የሚያከብሩት ሳምንት ነው፡፡
በሁነቱ ላይ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚካሄዱ ሲሆን በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ የASEB (Africa Startup Ecosystem Builders) ሽልማት፣ በመዝጊያው ዕለት ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢንተርፕሪነርሽፕ ሥነ ምኅዳር ላይ አስተዎጽዖ ያላቸው ባለድርሻዎች እውቅና የሚያገኙ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ 4 ሺህ 375 ተግባራት በማስቆጠር ከብራዚል ቀዳሚ ሆና ዓለም አቀፍ መሪ መሆኗን የዓለም አቀፉ የኢንተርፕሪነርሽፕ ሳምንት (GEW) ድረ-ገጽ ይፋ ባደረገው የደረጃ ሰንጠረዥ (Leaderboard) ላይ ተገልጿል።
በሃበነዮም ሲሳይ