በሰውነት ውስጥ የሚገኙ ሴሎች ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መንገድ በብዛት መመረት የካንሰር ቫይረስ እንዲፈጠር ያደርጋል፤ ቫይረሱም በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በመሰራጨት ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡
የካንሰር ሴሎች በአብዛኛው በአንድ ቦታ ላይ የሚጠራቀምና አጢ መሳይ እድገት ሲኖረው ቀሪው በደምና በሌሎች የሰውነት ፈሳሽ ማዘዋወሪያ ቱቦዎች በኩል በመላ ሰውነት በመሰራጨት ሰውነትን ያጠቃል፤ አለፍ ሲል ለሞት ይዳርጋል፡፡
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በዓለም ላይ በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች በ4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ሴቶችን የሚያጠቃ የካንሰር ህመም ዓይነት እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጂ የማህፀንና ጽንስ ስፒሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ፍላጐት ታደሰ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ከ90 እስከ 95 በመቶ “ሁማንፓኘሎማ” በተሰኘ ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ከሌሎች ካንሰር በተለየ መልኩ በመከላከል መቆጣጠር እንደሚቻል እና በሽታው ከተከሰተ በኋላም ቢሆን ሥር ሳይሰድ ከታወቀ በህክምና የሚድን በሽታ ነው ብለዋል፡፡
ቫይረሱ ልቅ በሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፍ ሲሆን፣ የማህፀን በር አካባቢ የሚገኙ ሴሎችን በመውረር ጤናማ ያልሆኑ ሴሎችን እንዲመነጩ በማድረግ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር እንዲፈጠር ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
ከ2ዐ ዓመት ቀደም ብሎ የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመር፣ ከተለያዩ ወንዶች ጋር የግብረስጋ ግንኙነት መፈፀም፣ የበሽታ መከላከል አቅም መቀነስ፣ የአባለዘር በሽታ እና ሲጃራ ማጨስ ለማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ህመም መንስኤ መሆናቸውን ዶ/ር ፍላጐት ታደሰ ገልፀዋል፡፡
በሽታው ምንም አይነት ምልክት ሳያሳይ ከ15 እስከ 2ዐ አመት ሊቆይ የሚችል በመሆኑ በየ 5 አመቱ ቅድመ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት ዶ/ር ፍላጐት ፡፡

በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት ደም መፍሰስ፣ ከመሀፀን የሚወጣ መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ፣ ህመሙ እየተባባሰ ሲሄድ የማህፀን፣ የወገብ እና የእግር ህመም የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ምልክቶች መሆናቸውንም ዶክተሯ ተናግረዋል፡፡
በሽታውን በክትባት፣ የግብረ ስጋ ግንኙነትን ከ2ዐ አመት በታች ባለመጀመር፣ ከልቅ የግብረስጋ ግንኙነት በመቆጠብ እና ሲጃራ ባለማጨስ እንዲሁም በየአምስት አመቱ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራ በማድረግ መከላከል ይቻላል፡፡
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር 4 ደረጃዎች ያሉት ሲሆን ደረጃው ከፍ እያለ በሄደ ቁጥር ህክምናው ውስብስብ ይሆናል፤ የመዳን እድሉም እየቀነሰ ይሄዳል፡፡
እንደየ ካንሰሩ ደረጃ በህመሙ የተጠቃውን አካል በቀዶ ጥገና ማስወገድ፣ የጨረር ህክምና፣ ኪሞ ቴራፒ እና ኢሚኖ ቴራፒ እንክብሎችን በመጠቀም በሽታውን ማከም እንደሚቻል ዶ/ር ፍላጐት ታደሰ አስገንዝበዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው