ሳይጫወቱ ብቁ ተጨዋቾች ማፍራት የቻሉት ሰባስቲያን ዲሳብሬ

You are currently viewing ሳይጫወቱ ብቁ ተጨዋቾች ማፍራት የቻሉት ሰባስቲያን ዲሳብሬ

AMN – ህዳር 08/2018 ዓ/ም

ትውልድና እድገታቸው ፈረንሳይ ቢሆንም አፍሪካን ጥንቅቅ አድርገው ነው የሚያውቁት፡፡ ምክንያቱም የእድሜ እኩሌታቸውን ያሳለፉት በአህጉሪቱ ነው፡፡

የ49 ዓመቱ ሰባስቲያን ዲሳብሬ እንደ አብዛኞቹ ፈረንሳውያን እግር ኳስን ተጫውተው አላሳለፉም፡፡

በአሰልጣኝነት ግን የሚታይ ስኬት አስመዝግበዋል፡፡

የኮትዲቯሩ አሴክ ሚሞሳስ ቀዳሚው የአፍሪካ ክለባቸው ነው፡፡ በአቢጃን መቀመጫውን ያደረገውና በርካታ ስኬታማ ተጨዋቾችን ያፈራውን ክለብ ለሁለት ዓመታት መርተው ስኬታማ አድርገውታል፡፡

ከዚያ የካሜሮኑን ኮተን ስፖርት፣ የቱኒዚያውን ኢስፕራንስ ዲቱኒስ፣ የአንጎላውን ሪክሪቲቮ ዶ ሊቦሎን፣ የአልጄሪያውን ጄ ኤስ ሳውራን፣ የሞሮኮውን ዋይዳድ ካዛብላንካ፣ የግብጾቹን ኢስማይሊና ፒራሚድ በዋና አሰልጣኝነት መርተዋል ጎልማሳው ዲሳብሬ፡፡

ከነዚህ ክለቦች ጋር ያስመዘገቧቸው ስኬቶች ለኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ኃላፊነት አበቃቸው፡፡ በኡጋንዳ የሁለት ዓመታት የመሪነት ዘመናቸው ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን ገንብተው አሳይተዋል፡፡

የቫሌንስ ከተማ ተወላጁ ሰባስቲያን ዲሳብሬ ከፈረንጆቹ 2022 ወዲህ ደግሞ የዲሞክራቲክ ኮንጎ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ዲሳብሬ ሀገሪቱን ከተረከቡ ወዲህ አዳዲስ ክብረወሰኖች አስመዝግበዋል፡፡ የ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ አንዱ ስኬታቸው ነበር፡፡

በወቅቱ በአሳማኝ ብቃት ለግማሽ ፍጻሜ ደርሰው በአስተናጋጇ ኮትዲቯር 1ለ0 ተሸንፈው ከፍጻሜው ውጭ መሆናቸው ይታወሳል፡፡

ለደረጃ በተደረገ ጨዋታ በደቡብ አፍሪካ በመለያ ምት ተሸንፈው በአራተኛነት በማጠናቀቃቸው በሀገሪቱ ፕሬዚደንት ፌሊክስ ሺሴኬዲ ከፍተኛ ሽልማት ማግኘታቸው አይዘነጋም፡፡

በቅርቡ ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ በኢትዮጵያ ምድብ የነበረችው ዲሞክራቲክ ኮንጎ የበላይ ሆና ጨርሳ ለመድረኩ በቅታለች፡፡ ለ2026ቱ የዓለም ዋንጫም ለማለፍ ጉዞ ላይ ትገኛለች፡፡

ዲሞክራቲክ ኮንጎ ምድቧን በሴኔጋል ተበልጣ በሁለተኛነት በመጨረሷ ለጥሎ ማለፍ ጨዋታ በቅታ ነበር፡፡

ባሳለፍነው ሐሙስ ከካሜሮን ጋር በጥሎ ማለፍ የተገናኘችው የመካከለኛው አፍሪካዋ ሐገር በተጨማሪ ደቂቃ ባስቆጠረቻት ግብ 1ለ0 አሸንፋ ለትናንቱ ፍጻሜ ደረሰች፡፡

ተጋጣሚዋ ደግሞ ናይጄሪያ ነበረች፡፡ 120 ደቂቃውን 1ለ1 ጨርሰው በተሰጠ የመለያ ምት የዲሳርቤ ልጆች 4ለ3 አሸንፈው በኢንተር ኮንቲኔንታል ዋንጫ የአፍሪካ ተወካይ ሆነዋል፡፡

እንደ ቦሊቪያን የመሳሰሉ ሐገራት በሚሳተፉበት የመጋቢት ወር የኢንተር ኮንቲኔንታል ዋንጫ የአፍሪካ ተወካይ የሆነችው ዲሞክራቲክ ኮንጎ ከስድስቱ ሐገራት ለፍጻሜ ከደረሰች፣ በ1974 በቀድሞ ስያሜዋ ‹‹ዛየር›› ከተሳተፈች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመድረኩ ትበቃለች፡፡

ለዚህ ስኬት ደግሞ ሳይጫወቱ ብቁ ተጨዋቾች ያፈሩት ዝምተኛው አሰልጣኝ ሰባስቲያን ዲሳብሬ ቀዳሚው ተወዳሽ ናቸው፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review