ለአመራሮች እና ለደንብ አስከባሪ ኦፊሰሮቹ የ2018 ዓ.ም ወታደራዊ እና የስነ-ምግባር ስልጠና መሰጠት መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታወቀ።
ስልጠናውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የሚሰጥ ሲሆን የአመራሮቹን እና የኦፊሰሮቹን ወታደራዊ እና ስነ-ምግባራዊ አቅም የሚያሳድግ መርሃ-ግብር ነው።
የስልጠና ማስጀመሪያ መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ የደንብ ማስከበር ባለስልጣንን አሁን ካለበት በተሻለ መልኩ ለማዘመንና ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል። ይህ ስልጠናም የተቋሙን አቅም ለማሳደግ ያግዛልም ነው ያሉት።
በተለይም ተቋም ግንባታ ላይ ትኩረት በማድረግ የመልካም አስተዳደርና የብልሹ አሰራር ችግሮችን የመለየትና አፈታታቸው ላይ ትኩረት ያደረገ በስነ-ምግባር እንዲሁም በአካል ብቃት የታነፀ ደንብ አስከባሪ መፍጠር ነው ብለዋል።
በመርሀ ግብሩ የንድፈ ሀሳብ፣ የባህሪ፣ የቴክኖሎጂና መሰል ስልጠናዎች የሚሰጡ መሆኑን የተጠቀሰ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ6ሽ በላይ ሰልጣኞች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።
ስልጠናው ሰንዳፋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፓሊስ ዩኒቨርስቲ ለሁለት ወር የሚሰጥ ሲሆን ሰልጣኞቹ በተለያየ መልኩ እራሳቸውን እንዲያበቁ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በንጉሱ በቃሉ