የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በጋዛ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ኃይል እንዲሰማራ ድምፅ ሊሰጥ ነው

You are currently viewing የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በጋዛ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ኃይል እንዲሰማራ ድምፅ ሊሰጥ ነው

AMN- ህዳር 8/2018 ዓ.ም

ረቂቅ የመፍትሄ ሀሳቡ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ኃይል በጋዛ እንዲሰማራ የሚፈልግ እና የጋዛን መልሶ ግንባታ ለመደገፍ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በዛሬው ዕለት በዶናልድ ትራምፕ የጋዛ የሰላም እቅድ በተለይም ዓለም አቀፍ ኃይል ማሰማራትን የሚያጠናክር ውሳኔ ላይ ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅቷል፡፡

የዚህ ውሳኔ ዋነኛ ምክንያትም፣ እርምጃ አለመውሰድ ጦርነቱ እንዲያገረሽ ሊያደርግ ይችላል ስትል አሜሪካ በማስጠንቀቋ ነው።

በከፍተኛ ድርድር ምክንያት በተደጋጋሚ የተሻሻለው ረቂቅ የመፍትሄ ሀሳቡ፣ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በፈረንጆቹ ጥቅምት 10 ላይ እንዲጀመር ተፈቅዶ የነበረውን የተኩስ አቁም ስምምነት ዕቅድ ተግበራዊ ያደርጋል ተብሏል።

ኤ ኤፍ ፒ አየሁት ባለው የረቂቁ ቅጂ መሰረት፣ ከእስራኤል እና ከግብፅ እንዲሁም ከአዲስ የሰለጠኑ የፍልስጤም ፖሊስ ጋር የድንበር አካባቢዎችን ለመጠበቅ እና ጋዛን ከወታደራዊ ኃይል ነፃ ለማውጣት የሚሰራ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ኃይል እንዲፈጠር ፈቃድ ይሰጣል።

ዓለም አቀፍ የፀጥታ ኃይል፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ የታጠቁ ቡድኖች የጦር መሳሪያዎችን በዘላቂነት በማስፈታት፣ ንፁሃንን መጠበቅ እና የሰብአዊ እርዳታ መተላለፊያዎችን ማስጠበቅ ላይ እንደሚሰራም ተመላክቷል።

በተጨማሪም፣ እስከ ፈረንጆቹ 2027 መጨረሻ ድረስ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ በትራምፕ ሊቀመንበርነት የሚመራው የጋዛ የሽግግር አስተዳደር አካል የሆነው “የሰላም ቦርድ” እንዲቋቋም ፈቃድ የመስጠት ስልጣን እንደሚኖረውም ተነግሯል።

ከቀደሙት ረቂቅ ዕቅዶች ይልቅ የአሁኑ በተለየ መልኩ የወደፊቱን የፍልስጤም ግዛት መፃኤ ዕድል ሊያመለክት ይችላል መባሉንም ቲ አር ቲ ዎርልድ ዘግቧል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review