አፍሪካ የተኩስ ድምጽ የማይሰማበት እህጉር እንድትሆን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ የአፍሪካ ህብረት ጥሪ አቀረበ

You are currently viewing አፍሪካ የተኩስ ድምጽ የማይሰማበት እህጉር እንድትሆን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ የአፍሪካ ህብረት ጥሪ አቀረበ

AMN ህዳር 9 /2018

አፍሪካ የተኩስ ድምጽ የማይሰማበት እህጉር እንድትሆን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ የአፍሪካ ህብረት ጥሪ አቅርቧል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የድህረ ግጭት መልሶ ግንባታ እና ልማት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት “ከግጭት በኋላ የዜጎችን ኑሮ በማካካሻ ፍትህ አማካኝነት በድጋሚ መገንባት” በሚል መሪ ሃሳብ ትላንት ተጀምሯል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ እ.አ.አ 2021 የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት በአህጉር ደረጃ እየሰፋ መምጣቱን ገልጸዋል።

ሳምንቱ ለአፍሪካ ህብረት የድህረ ግጭት መልሶ ግንባታ እና ልማት ፖሊሲ የፖለቲካ ድጋፍ ማግኛ፣ የአጋርነት ማጠናከሪያ እና የሀብት ማሰባሰቢያ ቁልፍ ማዕቀፍ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የዘንድሮው መሪ ሃሳብ በግጭት ውስጥ የነበሩ ማህበረሰቦች ፍትህን ማዕከል ባደረገ መልኩ እንዲያገግሙ ያለውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው ግጭት ያስከተላቸውን ሰዋዊ፣ ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ተጽእኖዎች መፍታት ሲቻል እንደሆነም ነው ሊቀ መንበሩ የገለጹት።

የጉዳት የካሳ ክፍያ፣ መልሶ ማቋቋም እና እርቅ ለሰላም ግንባታ ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውን አመልክተዋል።

የአፍሪካ መንግስታት፣ ቀጣናዊ ተቋማት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ምሁራን እና የልማት አጋሮች ሰላማዊ እና አይበገሬ ማህበረሰቦችን የመገንባት ስራን ለማጠናከር በትብብር እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የተሻሻለው የአፍሪካ ህብረት የድህረ ግጭት መልሶ ግንባታ እና ልማት ፖሊሲ ከፀደቀ ጊዜ አንስቶ የህብረቱ የዘርፉ ማዕከል በሽግግር ላይ ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።

ሊቀ መንበሩ የህብረቱ አባል ሀገራት ቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ በእርቅ እና በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች እያደረጉት ላለው ድጋፍም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ህብረት ማህበረሰቦችን የማብቃት፣ ሁሉን አቀፍ አስተዳደር እንዲሰፍን እና የአህጉሪቷ የረጅም ጊዜ የሰላም አጀንዳ ስኬታማ እንዲሆን በቁርጠኝነት ይሰራል ነው ያሉት።

ሁሉም አጋሮች አፍሪካ የተኩስ ድምጽ የማይሰማበት እህጉር እንድትሆን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች እና የአጀንዳ 2063 ግቦች እንዲሳኩ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአፍሪካ ህብረት የድህረ ግጭት መልሶ ግንባታ እና ልማት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት እስከ ህዳር 14 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ተዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review