የትዉልድ ድምጽ የሆነዉ ኤ ኤም ኤን በያገባኛል ፕሮግራሙ ወቅታዊና አንገብጋቢ የሆኑ ጉዳዮችን በማንሳት ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመምከር የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያመላክታል፡፡
በዚህ ሳምንትም የዜጎች የመማር ፍላጎት፤ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እና የዉጤት መታጣት እንዴት ይታያል ሲል የአዲስ አበባ ነዎሪዎችን አገጋግሯል።
ወጣት ደቻሳ ገለታ የማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀም በተማሪዎች ዉጤት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠሩን ይናገራል፡፡
ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች ከጥናት ይልቅ ጊዜአቸዉን ቲክቶክና ፌስቡክን የመሰሉ የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞችን በመጎብኘት ያሳልፋሉ ፤ ይህም ትምህርታቸዉን ትኩረት ሰጥተዉ እንዳይከታተሉ ከፍተኛ ተግዳሮት ፈጥሯል፡፡
ወይዘሮ ተዋበች ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው አንዳንድ ልጆች በማህበራዊ ሚድያ ላይ በሚለቀቁ ይዘቶች በመማረክ ትምህርታቸዉን እንደሚዘነጉ ነዉ የሚገልጹት፡፡

በፌስቡክ ፤ በቲክቶክ እና በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ መረጃዎችም በተማሪዎች ዉጤት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደሩ ነዉ፡፡
ተማሪዎች ስለትምህርት ከመወያየት ይልቅ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስለ ተለቀቁ መረጃዎች መነጋገርን ይመርጣሉ ፤ይህም ለትምህርት ያላቸዉን ተነሳሽነት ይቀንሳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያን ተጽእኖ የተረዱት ወይዘሮ ተዋበች ወልደጊዮርጊስ ልጃቸዉን ከተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በማራቅና ሞባይል በመከልከል ጭምር ትምህርቷ ላይ እንድታተኩር ማድረጋቸዉን ገልጸዋል፡፡
ልጆችን ከማህበራዊ ሚድያ በትንሹም ቢሆን እንዲርቁ በማድረግ ትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ካላደረግናቸው በስተቀር ፣ አገር ተረካቢ ትዉልድ ልናጣ እንችላለን የሚሉት ደግሞ አቶ ሻሽ ሀሰን ናቸዉ፡፡
ልጆች ሞባይል እና ማህበራዊ ሚዲያዎችን ያለ ገደብ እንዲጠቀሙ ወላጆች መፈቀድ የላባቸዉም ፤ ከትምህርት ጋር ተያያዥነት ያላቸዉን መረጃዎች ሲጠቀሙ ክትትል ማድረግ ይገባል ብለዋል።
አቶ ናትናኤል ሽፈራው እንደሚገልጹት ከሆነ ተማሪዎች ጊዜአቸዉን ከትምህርት ይልቅ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የሚያሳልፉ ከሆነ የዉጤት መቀነስ ሊያጋጥማቸዉ ይችላል፡፡ ይህም ተምረው የስራ ዕድል የማያገኙበት ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች በተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ አማራጮች የምዕራቡን አለም ታሪክ እና የአኗኗር ዘይቤ በማየት ለነገዉ ህይወታቸዉ መሰረት ሳይጥሉ ይቀራሉ፡፡
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ እስክንድር ጀንበሬ( ዶ/ር) ጥናቶችን እና ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎችን ዋቢ አድርገው እንደገለጹት ከሆነ አንዳንድ ተማሪዎች ለትምህርት የሚሰጡት ዋጋ አነስተኛ በመሆኑ በፈተና የማለፍ ምጣኔ እየቀነሰ መጥቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የመሰረት ልማት አለመሟላት ፣ የመምህራን ብቃት ማነስ እና ሌሎች ምክንያቶች በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ችግሮች እንደሚፈጥሩ አመላክተዋል።
የትምህርት ፍላጎት መቀነስ በተማሪዎች ዉጤት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ያሳድራል፤ ይህም ተማሪዎች ለትምህርት የሚሰጡት ዋጋ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡
በትምህርት ጥራት ላይ የሚነሱ ዘርፈ ብዙ ማነቆዎችን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጥምረት ሊሰሩበት እንደሚገባም የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር እስክንድር ጀንበሬ( ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በሔለን ተስፋዬ