የአውሮፓ ሀገራት የ2026 የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጠናቀቁ ተጨማሪ አምስት ሀገራት በቀጥታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
በምድብ ሦስት አስደናቂ ፉክክር የተደረገበት የስኮትላንድ እና ዴንማርክ ጨዋታ በስኮትላንድ 4ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ስኮትላንድ ከ28 ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ መድረክ ተመልሳለች።
በሀምፕደን ፓርክ በተደረገው ጨዋታ የስኮትላንድን የድል ግቦች ስኮት ማክቶሚኔ ፣ ሎውረንስ ሻንክላንድ ፣ ኬረን ቴርኒ እና ኬኒ ማክሊን ማስቆጠር ችለዋል።
ራስመስ ክሪስታንሰንን በቀይ ካርድ ላጡት ዴንማርኮች ራስመስ ሆይሉንድ እና ፓትሪክ ዶርጉ ሁለቱን ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል።
በቀጥታ የማለፍ እድሏን ያልተጠቀመችው ዴንማርክ በጥሎ ማለፍ የምትሳተፍ ይሆናል።
በምድብ አምስት የተደለደለችው ስፔን ከቱርኪዬ ጋር 2ለ2 በመለያየት የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ሆናለች።
ለስፔን ዳኒ ኦልሞ እና ሚካኤል ኦያርዛባል ፣ ለቱርኪዬ ዴኒዝ ጉል እና ሳሊህ ኦዝካን ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ቱርኪዬ 2ኛ ደረጃ ይዛ በማጠናቀቋ በጥሎ ማለፍ ዙር ትሳተፋለች።
በምድብ ሁለት ከኮሶቮ ጋር 1ለ1 የተለያየችው ስዊዘርላንድ የ2026ቱ ዓለም ዋንጫ ትኬቷን ቆርጣለች።
በምድብ ስምንት በተመሳሳይ ኦስትሪያ ከቦስኒያ 1ለ1 በመለያየት የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ሆናለች።
ሊችተንስታይንን 7ለ0 ያሸነፈችው ቤልጂየም በ2026 የዓለም ዋንጫ ሌላኛዋ አውሮፓን የምትወክል ሀገር ሆናለች።
በሸዋንግዛው ግርማ