በሰመራ ሎጊያ ከተማ ሲካሄድ በቆየው 10ኛው የከተሞች ፎረም ማጠናቀቂያ መልዕክት ያስተላለፉት ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የክትመትና የስልጣኔ ታሪክ ቢኖራትም ከተሞችን በዘላቂ ስትራቴጂ የመምራትና መሰረተ ልማት የማስተሳሰር ውስንነት እንደነበር አስታውሰዋል።
የመደመር መንግስት ከተሞችን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተመስገን እንደ ሰርቶ ማሳያና የብዝሀ ዘርፋ ማበብያ ተደርገዋል ብለዋል።
በየ2 አመቱ የሚካሄደው የከተሞች ፎረምም ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ሽግግር ከተሞች ግንባር ቀዳም ተደርገው ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

አዲስ አበባ የጀመረው የኮሪደር ልማትም በሌሎች ከተሞችና ገጠሮች በመስፋት እየተሳሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የመሬት አስተዳደርን ማዘመን ገቢን መሰብሰብ መሰረተ ልማትን ማዘመን ገዥ የወል ትርክትን መገንባት ኢንዱስትሪን ማስፋፋት ቱሪዝምን በማላቅ ከተሞች ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ነው አቶ ተመስገን ያስገነዘቡት።
የከተሞች ፎረምም በመካከላቸው ጤናማ የውድድር መንፈስ እንዲፈጠር በማድረግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
ከተሞች በቀጣይም የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን መጨመር ፣ጽዳትና አረንጓዴ ልማትን መስራት ፣በየአካባቢያቸው የሚገኙ ታሪካዊ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን የቱሪዝም መስህብ ማድረግ እንዲሁም ወጣቶችን የ5 ሚሊየን ኮደርስ ስልጠና ተጠቃሚ በማድረግ የነገ ኢንዱስትሪያሊስቶችን ማብቃት ይገባል ብለዋል።
በፍቃዱ መለሰ