ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ አቅም በመጠቀም በላቀ የኢኮኖሚ ዕድገት እየተጓዘች ነው

You are currently viewing ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ አቅም በመጠቀም በላቀ የኢኮኖሚ ዕድገት እየተጓዘች ነው

AMN ሕዳር 10/2018

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ያላትን ዕምቅ አቅም በመጠቀም በላቀ የኢኮኖሚ ዕድገት እየተጓዘች ነው ሲሉ የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሴሪ አንዋር ኢብራሂም ገለጹ።

የኢትዮጵያ ማሌዢያ ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል በተካሄደው ፎረም ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ፣የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሸን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)ን ጨምሮ የሀገራቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የንግድና ኢንቨስትመንት አልሚ ባለሀብቶች ተገኝተዋል።

የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሴሪ አንዋር ኢብራሂም፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም ውስጥ አድናቆት የተቸራት ታላቅ ሀገር መሆኗን እንደሚያውቁ ገልጸዋል።

ለዚህም ነብዩ መሐመድ ወደ ሐበሾች ምድር የላኳቸውን የመጀመሪያ ሙስሊም ስደተኞች የክርስቲያን ንጉስ በፍቅርና አክብሮት እንደተቀበላቸው አስታውሰዋል።

ይህ ዓይነቱ ታሪክም በመረዳዳትና ዕውቀት ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ወሳኝ ትምህርት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮ-ማሌዢያን ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር የጋራ ትብብሮችን ማስፋት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የዲጂታል ሽግግር፣ የዳታ ዘርፍ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት መሠረታዊ የኢኮኖሚ ማሳለጫ የመፍትሔ መንገዶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያም ባለፉት ዓመታት ያላትን ዕምቅ አቅም በመጠቀም በላቀ የኢኮኖሚ ዕድገት እየተጓዘች መሆኗን ጠቁመው፤ ይህም የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።

የማሌዢያ የፖለቲካዊ መረጋጋት ከኢንዱስትሪ ማስተር ፕላን እስከ የኢነርጂ ሽግግር፣ የመንገድ ካርታ እስከ ዲጂታል ሽግግር ስትራቴጂና መሠረተ ልማት ግንባታ ድረስ በወጪ ንግድ ጠንካራ ሀገር መሆኗን አስረድተዋል።

የማሌዢያ የንግዱ ማህበረሰብ ልዑካን ተሳትፎ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ግንኙነታችንን ለማጠናከር ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው ብለዋል።

የሀገራቱን ትብብርም እንደትልቅ ዕድል በመጠቀም በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ማስገንዘባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ለተደረገላቸው የላቀ የእንግዳ አቀባበል ደማቅ ሥነ-ስርዓት ምስጋና አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review