ደም ግፊት የሚባለው ልብ ወደ ተለያዩ የሰውነት ህዋሶች ደም በሚረጭበት ወቅት በደም ሥሮች ግድግዳ ላይ የሚፈጠር ኃይል ነው።
ልብ ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ደም በሚረጭበት ወቅት ከአቅም በላይ ደም ለመርጨት የሚያጋጥም ኃይል ወይም ሞገድ ደግሞ የደም ግፊት በሽታ ይባላል። የደም ግፊት በደም ወሳጅ የደም መስመሮች ውስጥ ዝውውር የተቀላጠፈ እንዲሆን የሚፈጠር ግፊት ነው።
የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት ከፍተኛ የደም ግፊት ትኩረት የሚሰጠው የጤና ችግር ሲሆን፣ ከልብ፣ ከአዕምሮ፣ ከኩላሊት እና ሌሎች የጤና ችግሮች ሊያጋልጥ የሚችል መሆኑን ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ የከፍተኛ ደም ግፊት ስርጭት 16 በመቶ ሲሆን፣ በከተሞች ደግሞ 22 በመቶ መሆኑን በዘርፉ የተሰሩ ጥናቶች ያመላክታሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የደም ግፊት ስርጭት 22.1 በመቶ ሲሆን፣ በወንዶች 25 በመቶ እንዲሁም በሴቶች ደግሞ 18.8 በመቶ የስርጭት መጠን እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ። ለከፍተኛ የደም ግፊት አጋላጭ ሁኔታዎች ሰዎች ሊቆጣጠሩት የሚችሉት እና ሊቆጣጠሩት የማይችሉት ተብለው በሁለት ተከፍሏል።
ጤናማ የሆነ አመጋገብ፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ አልኮል አለመጠጣት እና ሲጋራ አለማጨስ ከፍተኛ የደም ግፊት መቆጣጠር የሚቻልበት ሁኔታዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
ከሰዎች ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ለከፍተኛ የደም ግፊት አጋላጭ ሁኔታዎች ደግሞ፣ በዘር ወይም ከቤተሰብ፣ በእድሜ፣ በግለሰቡ ላይ የስኳር፣ የኩላሊት፣ ከልብ ጋር ተያያዥ የሆኑ የጤና ችግር መኖር ዋነኞቹ ናቸው።
አብዛኛው ጊዜ ከፍተኛ የደም ግፊት ምንም ዓይነት ምልክት ላያሳይ እንደሚችል እና ምልክት ከተከሰተ የሚታየው የጠዋት ራስ ምታት፣ ነስር፣ የተዘበራረቀ የልብ ምት፣ የእይታ መታወክ፣ የጆሮ መጮህ ምልክቶች ሊሆን ይችላል። በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰ ደግሞ ድካም፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ ግራ የመጋባት፣ ጭንቀት፣ የደረት ህመም እና የመተንፈሻ ችግር ምልክቶቹ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመላክቷል።
ከፍተኛ የደም ግፊት መቆጣጠር ካልተቻለ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ተፅዕኖ ያስከትላል። ከሚያስከትላቸው ተፅዕኖዎች ውስጥ የስኳር ህመም፣ የኩላሊት ጉዳት፣ ስትሮክ ወይም የአንጎል የደም ዝውውር መታወክ፣ የልብ ድካም/ህመም፣ የደረት ውጋት/ህመም እና የዓይን ሕመም ናቸው ።
ከፍተኛ የደም ግፊት ለማከም ሁለት መንገዶች ያሉት ሲሆን፣ የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል አንደኛው አማራጭ ነው። ጤናማ የሆነ አመጋገብን መከተል፣ የጨው መጠን መቀነስ፣ ክብደት መቀነስ፣ ሲጋራ አለማጨስ እና ከሚጬስበት ስፍራ መራቅም ከመጀመሪያው አማራጭ መካከል ይገኝበታል።
ሁለተኛው ደግሞ፣ የበሽታው ሁኔታ በሀኪም ከተረጋገጠ በኋላ የሚታዘዙ መድሃኒቶችን በአግባቡ በመጠቀም የግፊት መጠንን ማስተካከል ሌላኛው መፍትሔ ነው።
እነዚህ መድሀኒቶች ከከፍተኛ የደም ግፊት የተነሳ የተለያዩ የሰውነት አካል ክፍሎች ተጨማሪ ጉዳት እነዳይደርስባቸው ለመከላከል የሚያግዙ መሆናቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በሔለን ተስፋዬ