ኢትዮጵያ የተገበረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በሁሉም የአገልግሎት ዘርፎች አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በመንግስት ድጋፍ ሰጪነት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረገች ሲሆን፣ ለዚህም አስፈላጊውን መሰረተ ልማት እና ግብዓቶች በማሟላት ተስፋ የተጣለባቸው ስራዎችን እየከወነችም ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በ2013 ዓ.ም የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በኢትዮጵያ ማስጀመራቸው ፋና ወጊ መሪ ያደርጋቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ አርቴፊቺአል ኢንተሊጀንሰ ኢንስቲቲዩትን በጎበኙበት ወቅት እንዳስታወቁት፣ ኢንስቲትዩቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለጤና፣ ለግብርና እና ለተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች መጠቀም የሚያስችሉ ሰፋፊ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን በመጠቆም፣ በክላውድ ኮምፒዩቲንግ፣ በትላልቅ የመረጃ ቋቶች፣ዳታ ማእከል፣ ሮቦቲክስ እና አመርቂ ቴክኖሎጂዎች አቅምን እያዳበሩ እንደሚገኙ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አፍሪካ ውስጥ ካሉ ታዋቂ እና ተጽእኖ ፈጣሪ የ (ኤአይ) ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢንስቲትዩቱ፣ ካከናወናቸው ዋና ዋና ስኬቶች መካከልም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጡት ካንሰርን መለየት የሚችል ቴክኖሎጂ የባለቤትነት መብት ማግኘት መቻሉንም አብራርተዋል።
ከብዙ በጥቂቱ ኢንስቲትዩቱ ካሳካቸው ግኝቶች አንዱ፣ የቡና በሽታን መለየት የሚችል አሰራር መዘርጋቱንም አረጋግጠዋል።
መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት የአሰራር ሥርዓትን በመተግበሩ፣ በአንድ ጊዜ ከ100 በላይ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሥርዓት መዘርጋቱን እና በዚህም የተገልጋዮች ምሬት እየተቀረፈ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መንግስት ኢንስቲትዩቱን ያቋቋመው ከ5 ዓመታት በፊት መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ጥቂት አመታት ውስጥ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እገዛ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አስታውቀዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳስገነዘቡት፣ ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የመጠቀም ፍላጎቱ እያደገ መምጣቱ እና በዚህም አመርቂ የሆነ ውጤት እየተመዘገበ በመሆኑ፣ በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በተለያዩ ዘርፎች በመተግበር ላይ እንደምትገኝ ይፋ አድርገዋል።
ኢንስቲትዩቱ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ላይ ያተኮሩ የክረምት ካምፕ የስልጠና መርሃ ግብሮችን በማቅረብ ወጣቶችን በማበረታታት ላይ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ኢንስቲቲዩቱ ላለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት ወጣቶችን በክረምት መርሐ-ግብር ሲያሰለጥን መቆየቱን ገልጸው ፤ ተቋሙ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የማስተርስ እና የዶክትሬት ዲግሪ ኘሮግራም በዩኒቨርስቲ ደረጃ እንዲሰጥም ትልቁን ድርሻ አበርክቷል ።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በሁሉም ዘርፍ ሊተገበር የሚችል እንደሆነና በተለይም ዛሬ ላይ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ የሰዎችን የስራ ጫና ለመቀነስ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ተቋሙ አሁን ላይ የግል እና የመንግስት ተቋማት የራሳቸው የመረጃ ቋት እንዲኖራቸው እየሰራ ይገኛል። ለዚህም በማሽን መነበብ የሚችሉ አምስት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን በመምረጥ ከጽሑፍ ወደ ጽሑፍ እና ከጽሑፍ ወደ ድምጽ እንዲገለብጥ ለማድረግ ተቋሙ እየሰራ መሆኑንም ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል።
ምንም እንኳን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሰውን መተካት ባይችልም፣ የሰውን ልጅ ድካም ከመቀነስ እና ውጤታማነት ከማሳደግ አንፃር ወደር የሌለው እና አይተኬ ሚና እንዳለውም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከ5 ዓመታት በፊት የሰው ሰራሽ አስተውሎት በእርሻ ፣ በኢንዱስትሪ፣ በጤና እና በአገልግሎት ዘርፎች ላይ የላቀ አበርክቶ እንደሚኖረው ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2050 በአለማችን ካሉ 20 ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገራት መካከል አንዷ ለመሆን ተግታ እየሰራች መሆኑም ተመላክቷል።
በወርቅነህ አቢዮ