ሩሲያ እና ቶጎ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

You are currently viewing ሩሲያ እና ቶጎ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
  • Post category:አፍሪካ

AMN- ህዳር 11/2018 ዓ.ም

ለ65 ዓመታት የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሩሲያ እና ቶጎ እስከ አሁን አንዳቸው በሌላኛው ሀገር ኤምባሲ ሳይከፍቱ ቆይተዋል።

ይሁንና የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በትናንትናው ዕለት እንዳስታወቁት፣ በሚቀጥለው ዓመት አንዳቸው በሌላኛው ሀገር ኤምባሲያቸውን ይከፍታሉ።

የሩሲያ እና ቶጎ ግንኙነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያደገ የመጣ ሲሆን፣ በተለይም በዚህ ዓመት የመከላከያ ትብብር ስምምነት ካደረጉ በኋላ ግንኙነታቸው ይበልጥ መጠናከሩን ቲአርቲ አፍሪካ ዘግቧል።

ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ከጀመረ 65 ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ እስከ አሁን አንዳቸው በሌላኛው ሀገር ኤምባሲ አለመክፈታቸውን የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን፣ ሞስኮን እየጎበኙ ላሉት የቶጎ መሪ ፋውሬ ግናሲንግቤ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በሚቀጥለው ዓመት ኤምባሲዎቻችንን ለመክፈት ስምምነት ላይ ደርሰናል ሲሉም ፑቲን አክለዋል።

ግናሲንግቤ በበኩላቸው፣ ሩሲያ ለቶጎ ተማሪዎች የትምህርት እድል በማመቻቸቷ አመስግነው፣ ኤምባሲዎቹ ከተከፈቱ በኋላ በመስኩ የበለጠ መስራት እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በፈረንጆቹ ነሐሴ ወር፣ ሩሲያ ከሶስቱ የሳህል ቀጣና ሀገራት ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ጋር የመከላከያ ትብብር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟ ይታወሳል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review