በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚደረጉ ምርጫዎች እና በኋለኛው ሕይወት ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖዎች

You are currently viewing በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚደረጉ ምርጫዎች እና በኋለኛው ሕይወት ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖዎች

AMN – ህዳር 12/2018 ዓ.ም

በ30ዎቹ ዕድሜዎ ከ15 ደቂቃ የእግር ጉዞ እስከ መደበኛ እንቅልፍ ማግኘት ያሉት ሂደቶች በእርጅና እድሜዎ ጤናማ ሆነው እንዲቀጥሉ ሊረዳዎ እንደሚችል የጥናት ውጤቶች ያመልክታሉ፡፡

በተለይም ወደ ሰማንያዎቹ የእድሜ ክልል ሲደርሱ፣ ከወጣትነትዎ ጊዜ ያነሰ ደካማ እና ምናልባትም በግንዛቤ ደረጃ በጥቂቱ የቀዘቀዘ ስሜት ሊሰማዎ ይችላል። የእንቅልፍ ልምድዎም ሊቀየር ይችላል፣ ይህም ምሽት ላይ የበለጠ እንቅልፍ እንዲወስድዎ እና ከዚያ ቀደም ብለው እንዲነቁ ያደርግዎታል።

ከሁሉም በላይ ግን፣ ቢያንስ አንድ የጤና እክል ሊያጋጥምዎትም ይችላል። ተመራማሪዎች ይህ የማይቀር ዕጣ ፈንታ እንደሆነ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አምነዋል።

በካሊፎርኒያ ባክ የተሰኘ ከዕድሜ መግፋት ጋር የተያያዘ ምርምር የሚያደርግ ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ኤሪክ ቨርዲን፣ “አሁን ባወቅነው መሠረት፣ አብዛኛው ሰው የአኗኗር ዘይቤውን ቢያሻሽል እስከ 90 ወይም እስከ 95 ዓመት ድረስ በጥሩ ጤንነት ሊኖር ይችላል” ብለዋል።

“ይህ ደግሞ አብዛኛው ሰው እስከ 65 ወይም 70 ዓመት ድረስ በጥሩ ጤንነት እየኖረ፣ ከዚያም እየታመመና በእርጅና ዘመን የሚያጋጥሙትን ችግሮች ሁሉ እየተቀበለ ካለበት ሁኔታ በእጅጉ የተለየ ይሆናል” በማለት አክለዋል።

በአመጋገብ መሻሻል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወይም አልኮልን በመቀነስ የጤና ሁኔታን ለማሻሻል በማንኛውም ዕድሜ መጀመር እንደማይረፍድ ቢናገሩም፣ ቶሎ መጀመር ግን የተሻለ ውጤት ያስገኛል ባይ ናቸው።

በተለይም 30ዎቹ ዕድሜዎች በርካታ የፊዚዮሎጂ ሥርዓቶች፣ ለምሳሌ የጡንቻ ብዛትና ጥንካሬ፣ የአጥንት ጥንካሬ ወይም የሜታቦሊክ ቁጥጥር፣ ከእድሜ ጋር የተያያዙ ጥቃቅን ለውጦችን ማሳየት የሚጀምሩበት ቁልፍ የዕድሜ ክልል እንደሆነ ተመራማሪዎች አጽንኦት ሰጥተዋል።

በሚኒሶታ የማዮ ክሊኒክ የኮጎድ የዕድሜ መግፋት ማዕከል የፊዚዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆአዎ ፓሶስ፣ “ይህ ወቅት የረጅም ጊዜ የመቋቋም አቅምን የሚገነቡ ልማዶችን ለማጠናከር እንደ ትልቅ ዕድል ሊወሰድ ይችላል” ብለዋል።

የእርጅናን ሂደት የሚያጠኑ ተመራማሪዎች ከተለመደው የእርጅና መንገድ የወጡ ሰዎችን በማጥናት የሚቻለውን ለማወቅ ይጥራሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ‘ማስተርስ አትሌቶች’ (Masters Athletes) ናቸው፤ እነዚህ ከ35 ዓመት በላይ የሆናቸው እና በመደበኛነት በአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦች ናቸው።

የእነዚህ አትሌቶች የእርጅና ሂደት ከብዙዎቻችን የተለየ እንደሆነ ዶ/ር ፖል ሞርጋን የተባሉ ባለሙያ ይገልፃሉ፡፡ በልብና የደም ዝውውር ስርዓት እና በጡንቻ ጥንካሬ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረስ፣ የጥንካሬ ማሽቆልቆል ሂደት ዘግይቶ ይታይባቸዋል።

“ይህ ተጨማሪ ‘መጠባበቂያ ኃይል’ (additional reserve) በመካከለኛው የሕይወት ዘመን እንደ መከላከያ ጋሻ ሆኖ ያገለግላል” ይላሉ ሞርጋን።

ባለሙያው እንደሚመክሩት፣ በጥሩ ሁኔታ ለማርጀት የተሻለውን ዕድል ለማግኘት፣ በተለይም ኤሮቢክስ እና የጡንቻ ጥንካሬ ላይ ትኩረት በማድረግ በ30ዎቹ ዕድሜ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ ይገባል።

የአካል ብቃትን እንደምንጠብቅ ሁሉ የአእምሮአችንን ጤና መጠበቅ፣ አልኮል መቀነስ እና ጥሩ የእንቅልፍ ባህል ማዳበር ተገቢ መሆኑን ያነሳሉ፡፡

በ30ዎቹ ውስጥ ለአመጋገብ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው። ፍራፍሬዎችና አትክልቶች፤ እንደ ካሮትና ማንጎ ባሉ ምግቦች ውስጥ የሚገኙትን የዕፅዋት ውጤቶችን መመገብ በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው፡፡

ተመራማሪዎች ያረጋገጡት ነገር ቢኖር፣ በወጣትነት ጊዜ የሚደረጉ ምርጫዎች በኋለኛው ሕይወት ላይ ዘላቂ ተጽእኖ አላቸው። በ30ዎቹ ጤናማ ልማዶችን ማቆየት ከሕይወት ዘመን በኋላ የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች፣ የአስተሳሰብ ችሎታ ማሽቆልቆል እና ድካም አደጋን ይቀንሳል ማለታቸዉን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review