ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ረገድ ከተማዋን የሚመጥን በስርዓት እና በህግ የሚመራ አሰራር ተዘርግቷል

You are currently viewing ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ረገድ ከተማዋን የሚመጥን በስርዓት እና በህግ የሚመራ አሰራር ተዘርግቷል

AMN – ህዳር 12/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ፣በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በአገልጋይ ፕረሮግራም የቀጥተ ስርጭት ከተመልካቾች ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አድማጭ ተመልካቾችም የመዲናዋን ሠላምና ጸጥታ የተመለከቱ ሃሳብ: አስተያየትና ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ለተነሱት ሃሳቦችና ጥያቄዎች ምላሽ የሠጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ረገድ ከተማዋን የሚመጥን በስርዓት እና በህግ የሚመራ አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

ለከተማዋ ሰላም ውጤታማነትም 1ሺህ 200 አዲስ የሰላም እጩ ሰራዊቶች፤ ከ23ሺህ በላይ የሚሆኑ ከነባሩ የሰላም ሰራዊት የተውጣጡ በአጠቃላይ 170ሺህ የሚደርሱ የሰላም ሰራዊቶች በሶስት ፈረቃ ተሰማርተው የከተማዋን ሰላም እና ጸጥታ እየጠበቁ እደሚገኙ አመላክተዋል፡፡

መርካቶ ከአሁን ቀደም ለዝርፊያና ስርቆት የተጋለጠ: ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የሚስተዋልበት የግብይት ቦታ እንደነበረ ገልጸዋል። አሁን ላይ ግን ህዝቡን በማሳተፍ በተሠራዉ ስራ ስርቆትና ህገወጥ ግብይትን በመከላከል ውጤታማ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል። ህገወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ የንግድ ሥርዓት በማምጣት ስኬታማ ስራ ተሰርቷል። ህጋዊ ነጋዴዎችን የማበረታታት ስራም እየተሰራ እንደሚገኝ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ አብራርተዋል።

በመርካቶ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማዎች አምራቹም ሆነ ሸማቹ በተረጋጋ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ እየተገበያየ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ገልጸዋል።

መዲናዋ በርካታ የዉጭ ሃገር ዜጎች እና ዲፕሎማቶች የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን የገለጹት ሃላፊዋ የውጭ ሀገር ዜጎች ህጋዊ ሰነድ እንዳላቸው የማጣራት እና ሰነድ ያላሟሉትን ለህግ የማቅረብ ስራ በተቋቋመዉ የጸጥታ ጥምር ሀይል እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ከቅድመ ማስጠንቀቅያ እና ፈጣን ምላሽ ጋር በተያያዘም መሻሻሎች መኖራቸዉን ጠቁመዋል።

ሰላም እና ጸጥታን ለማስከበር መረጃ ትልቅ አቅም አለው ያሉት ወ/ሮ ሊዲያ በከተማዋ በሚካሄዱ ትላልቅ ሁነቶች እና ህዝባዊ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው ስፍራዎች ጸረ ሠላም ሃይሎች ሊፈጥሩ የነበሩትን አደጋዎች በተደጋጋሚ ማክሸፍ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባ የኢኮኖሚ፤ የሰላም እና የጸጥታ ተምሳሌት ከተማ መሆኗን ገልጸው፤ ከሸገር ከተማ ጋር በመናበብ እና በቅንጅት በመስራታቸው ትልልቅ ህዝባዊ በዓላት በተሳካ ሁኔታ መካሄዳቸውን አመላክተዋል፡፡

በፍሬህይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review