ኢትዮጵያ በብልጽግና ጉዞ ላይ ለመሆኗ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ማሳያ ናቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር ገለጹ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ህዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ ከተማ አቀፋዊ የህዝብ ለህዝብ መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ የብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በዚሁ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር፣ አዲስ አበባ የሁሉም ብሄሮች እና ህዝቦች መገኛ በመሆኗ በዓሉ ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል ብለዋል።
ያለፉት የለውጥ አመታት በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች እምርታዎች የተገኙበት መሆኑን የጠቆሙት አፈ ጉባዔዋ፣ በእነዚሁ የለውጥ ዓመታት አካታች የሆነ እውነተኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት ተፈጥሯል ብለዋል።
ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች በሁሉም አካባቢ መዳረሳቸው የዚሁ እምርታ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።
ልማት የጋራ ጥረትን እንደሚፈልግ የጠቆሙት ወይዘሮ ቡዜና፣ ለመጻኢ የሀገር እጣፈንታ ሁሉም በመሳተፍ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ያለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ በትክክለኛ የብልጽግና ጉዞ ላይ መሆኗን የገለጹት አፈ ጉባኤዋ፣ ለዚህም አዲስ አበባ ዋነኛ ማሳያ ነች ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ትልቅ እምርታ ማሳየቷን ያመላከቱት አፈ ጉባኤ ቡዜና፣ በከተማዋ የብሔር ብሔረሰቦችን ውክልና በማረጋገጥ በኩልም ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን አክለዋል።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔሰሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል “ደሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ ይከበራል።
በሀብታሙ ሙለታ