ከስፖርት የተሻገረ እውቅና

You are currently viewing ከስፖርት የተሻገረ እውቅና

“እውቅናው በስፖርቱ ዘርፍ የሀገራችንን ብሎም የከተማችንን ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚያጎላ ነው”
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

ታላቁ ገጣሚና ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን፣ “አበበ እንጂ መቼ ሞተ”  በተሰኘ ግጥሙ “የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ፣

ያረጋት የኦሎምፒክ ዓርማ፡፡” እንዳለው፣ ጀግናው አበበ ቢቂላ ታሪኩ ከመቃብር በላይ ነፍስ እየዘራ፣ የሀገርን ዘመን እያደሰ፣ በዓለም አደባባይ መልሶ መላልሶ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያነገሰ ቀጥሏል፡፡

እውነትም “አበበ እንጂ መቼ ሞተ”   ይሄው ዛሬም ዓለም በአበበ ጀግንነት ለኢትዮጵያ እውቅና መስጠቱን ቀጥሏል።

አዎ! ዛሬም በአበበ አብበናል፤ በኃይሌ ኃይላችን ጨምሯል፡፡ ለዚህ ደግሞ ባሳለፍነው ሐሙስ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ፣ በአበበ ቢቂላ ዘመን አይሽሬ ጀግንነት እና በኃይሌ ገብረሥላሴ አጋፋሪነት በተጀመረውና ለ25 ዓመታት ለአዲስ አበባና ለዓለም ድምቀት በሆነው ‘ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ’ “የዓለም አትሌቲክስ ቅርስነት” እውቅናን ተቀብላለች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እውቅናውን በተቀበሉበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት እንዲህ አሉ፤ “ሩጫ በኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክና ቦታ አለው፡፡ ላለፉት 65 ዓመታት ኢትዮጵያ በርካታ የረጅም ርቀት ሯጮችን ለዓለም አበርክታለች”

በትክክልም ሩጫ በኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክና ቦታ አለው፡፡ ለዚህ ሀሳብ ማረጋገጫ ይሆነን ዘንድ እንደከረመ ወይን እያደር ከሚጣፍጠው የሻምበል አበበ ቢቂላ የታሪክ ማህደር ጥቂት ሰበዞችን እንምዘዝ፡፡

ኢትዮጵያውያን አርበኞች ደረታቸውን ለጦር፣ እግራቸውን ለጠጠር ሰጥተው በዓድዋ ተራሮች ግርጌ ለሀገራቸው ከፍታ እስከ ሞት ድረስ ታምነው እንዳስከበሩን ሁሉ ጀግናው ሻምበል አበበም በሮም በባዶ እግሩ ሮጦ የሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ በታላቅ ጀብዶ ከፍ አደረገ፡፡

ጣሊያናውያን በዓድዋ ተራሮች “የወደቅንበትን አንረሳም” ሲሉ እንደመሰከሩት ሁሉ  የክብር ዘበኛው ወታደር አበበ ሀገሩን ተሸክሞ በሰራው ታላቅ ጀብዱ “ሙሶሎኒ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን አሰልፎ፣  መድፍ እና መርዛማ ጋዝ ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ሲወር፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ወታደር ግን ጣልያንን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም አሸነፈ” በማለት በየሚዲያዎቻቸው ሁሉ ዘገቡለት።

ይህ የአልሸነፍ ባይነት፣ ታሪክና ገድል፣ ዝናና ወኔ ወደ እነ ምሩጽ ይፍጠር፣ ወደነ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ወደነ ደራርቱ ቱሉ፣ ወደነ ቀነኒሳ በቀለ፣ ወደነ መሠረት ደፋር፣ ወደነ ጥሩነሽ ዲባባ እና ፅጌ ዱጉማን በመሳሰሉ እልፍ ጀግኖች ደም ውስጥ በረቂቁ የሀገር ፍቅር ስሜት እየተላለፈ ዛሬም ቀጥሏል፡፡

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም ሐሙስ 10 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተከናወነው ዓለም አቀፍ እውቅና ላይ ባስተላለፉት መልዕክትም አበበ ቢቂላ በ1952 ዓ.ም በጣሊያን መዲና ሮም በተካሄደው 17ኛው የኦሎምፒክ ማራቶን ውድድር ላይ በባዶ እግሩ በመሮጥ እና የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት ታሪካዊ ድል ማስመዝገቡን በመከተል በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ጀግና አትሌቶች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረጋቸውን አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያገኘችው “የዓለም አትሌቲክስ ቅርስነት” እውቅና በስፖርቱ ዘርፍ የሀገራችንን ብሎም የከተማችንን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነትን የሚያጎላ ነው ያሉት ከንቲባዋ፣ ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላን፣ የታላቁ ሩጫ ውድድር መስራች የሆነውን ጀግናው አትሌታችን ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴን እና ይህንን ውድድር ባለፉት ዓመታት ባማረ ሁኔታ ሲያካሂዱ የቆዩትን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ማመስገን እወዳለሁም ብለዋል፡፡

ከንቲባዋ በዕለቱ ባደረጉት ንግግርም በቀጣይ ውድድሩን ከዚህም የበለጠ ለማሳደግ እና ብዙ የውጭ ሀገር ተሳታፊዎችን ወደ ከተማዋ እንዲያመጣ ለማድረግ የበለጠ በትብብር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡

ለመሆኑ ከንቲባዋ ለስፖርቱ ዘርፍ በተለይም “የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድርን ከዚህም በበለጠ ለማሳደግ እና ብዙ የውጭ ቱሪስቶችን ለመሳብ በትብብር እንሰራለን” ማለታቸውን መነሻ በማድረግ ይህን መሰል ውድድሮችን ማጠናከርና መደገፍ ለሀገርና ለከተማዋ ገፅታ ግንባታ እንዲሁም የቱሪዝም ኢኮኖሚውን ከፍ ለማድረግ ምን አበርክቶ አለው? ለሚለው ጥያቄ የቱሪዝም ኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ፍሬዘር አለሙ በሰጡን ምላሽ መንገዱና መልኩ  ቢለያይም የዲፕሎማሲ ዋና ማጠንጠኛውና ግቡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማላቅ ነው ብለዋል፡፡

የስፖርት ቱሪዝም ደግሞ በዓለም የተከፈተ አዲስ የኢኮኖሚ በር ነው። ለዚህ ደግሞ የአረብ ሀገራት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለስፖርቱ የሰጡት ትኩረትና ታላላቅ የዓለማችን ከዋክብት መዳረሻ መሆናቸውን፣ ይህንንም ተከትሎ ዓለም ወደነዚህ አካባቢዎች ፊቱን እያዞረ መሆኑን እና ይህም ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳው እንደተጠበቀ ሆነ በስፖርት ቱሪዝም እያስመዘገቡት ያለው ስኬት በቀላሉ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡

በመሆኑም ይላሉ የቱሪዝም ኢኮኖሚ ባለሙያው እንደ ታላቁ ሩጫ ያሉ በርካታ ህዝብ በአደባባይ ወጥቶ በነፃነት ስፖርታዊ ውድድሮችን የሚሳተፍባቸው መድረኮች ለአዲስ አበባ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከማስገኘታቸውም ባሻገር የከተማዋን ሁለንተናዊ ምቹነት እና በአጭር ጊዜ እያስመዘገበች ያለውን ለውጥ ዓለም የበለጠ እንዲያውቅ ዕድል ይፈጥራል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በርካታ ቱሪስቶች ወደ መዲናዋ ይመጣሉ፣ ከስፖርታዊ ውድድሮቹ ባሻገርም በከተማዋ ያሉ ልዩ ልዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን ይጎበኛሉ፤ ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹነት ያረጋግጣሉ፤ ይህም ለከተማዋም ሆነ ለሀገር ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ “የዓለም አትሌቲክስ ቅርስነት” እውቅናን እንድታገኝ አንዱ ምክንያት የሆነው ኢትዮጵያዊው ሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ ታላቁን የኦሎምፒክ ማራቶን በአንደኝነት ከማሸነፍም በተጨማሪ 2፡16፡2 በሆነ ሰዓት አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዘገበ። በኦሎምፒክ ታሪክ፣ የሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን የቻለ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ስፖርተኛ ሆኖ ስሙ በታሪክ መዝገብ በወርቃማ ቀለም ሰፈረ፡፡

በወቅቱም ጋዜጠኞች አበበ ለምን ያለ ጫማ በባዶ እግሩ እንደሮጠ ጠይቀውት ነበር፡፡ እሱም በኩራት እንዲህ አለ፡፡ “እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሌም የምናሸንፈው በጀግንነትና በወኔ እንደሆነ፤ ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ በመፈለጌ ነው”፡፡ ቀጠል አድርገውም፣ “የአክሱም ሃውልት የተተከለበት አደባባይ ላይ ስትደርስ ፍጥነትህን የጨመርከው ለምንድነው?” የሚል ጥያቅም አቅርበውለት ነበር፡፡ መልሱ ግን “ሃውልቱን ሳይ ቁጣ ስለተሰማኝ ነው” የሚል ነበር፡፡

በሚቀጥለው ዓመት በግሪክ፤ በጃፓንና በቼኮዝላቫኪያ በተደረጉ የማራቶን ውድድሮች ድልን የተጎናፀፈው ሻምበል አትሌት አበበ ከዚያ በኋላ ለበርካታ ወራት በዓለም አቀፍ ውድድሮች ባይካፈልም ስሙ ከዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማትና ሚዲያዎች አልጠፋም። ይሄው ዛሬም ሀገሩን በድጋሜ ለታላቅ ክብር አብቅቷል።

የማራቶኑ የምንጊዜም ጀግና ሻምበል አበበ ቢቂላን፣ ባለቅኔ ጸጋዬ ገብረመድኅን “አበበ እንጂ መቼ ሞተ!!” ሲል ባሰፈረው የቅኔ ጠብታው እንዲህ ይገልፀዋል፡፡

የምድር አለሙ ገሞራ

አገሩን በክብር ያስጠራ

ሳተናው እግረ ጆቢራ

ሎጋ ቢቂላ ዋቅጂራ፤

የጎበዛዝ ንጥረ ወዙ

የተስፋ ብርሃን መቅረዙ…።

አዎ! ሻምበል አበበ ቢቂላ ከዓድዋ ድል ቀጥሎ ጥቁር ነጭን ማሸነፍ የሚችል ጀግናና አይበገሬ መሆኑን ያስመሰከረ የተስፋ ብርሃን መቅረዝ ነው፡፡

በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ አፍሪካን ከባድ ድብርት ተጫጭኗት ነበር፡፡  ወቅቱ አውሮፓውያን የአፍሪካ ሀገራትን የወረሩበት፣ በአፍሪካ ምድር የነጻነት አየር ሽው ማለት ያቆመበትና በብዙ ሀገራትም ስቃይ ቤቱን የሰራበት ጊዜ ነበር፡፡ 

በዚያ ጨለማ ወቅት ከአፍሪካ ቀንድ ምድር ከሀገረ ኢትዮጵያ የአልደፈርም ባይነትና የነፃነት ችቦ ከፍ ብሎ ይታይ ነበር፡፡ የብርሃኑ ወጋገንም ለብዙዎች ተስፋና ወኔ ሆነ፡፡ ከሌሎች ድሎች ማግስትም የአህጉሪቱን ስፖርት የተጫነው የአፓርታይድ ትልቅ ቋጥኝም ተፈንቅሎ ወደቀ፡፡ የዚህ ደማቅ ታሪክ ፀሐፊ ደግሞ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ናቸው፡፡ ብዙዎችም የፀረ አፓርታይድ አጋፋሪ እና የአፍሪካ ጠበቃ ሲሉም ይመሰክሩላቸዋል፡፡ 

አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ በ“ፒያሳ ልጅ” መፅሐፋቸው እና “ጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ – የአፍሪካ ጠበቃ” በተሰኘው መጣጥፋቸው እንደገለፁት የአፍሪካን ስፖርት ነፃ ያወጡት ልክ እንደ አበበ ቢቂላ በስፖርቱ ዓለም ደማቅ ታሪክን ፅፈው ያለፉትን ኢትዮጵያዊው ጀግና የጋሼ ይድነቃቸውን ጉልህ አስተዋጽኦ ማስታወስ ይገባል፡፡

እነዚህና አያሌ ኢትዮጵያውያን ከዋክብት ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገዋታል፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያ ያገኘችው ዓለም አቀፍ እውቅና ብዙ ፋይዳ አለው፡፡ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እውቅናውን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክትም እውቅናው “በስፖርቱ ዘርፍ የሀገራችንን ብሎም የከተማችንን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነትን የሚያጎላ ነው” ብለዋል፡፡

ለዘመናት ያህል በዓለም መድረክ ኢትዮጵያን ከፍ ያደረጉ የአያሌ ጀግኖች ሀገር ሆነን በስፖርት ቱሪዝም እምብዛም አለመጠቀማችን የሚያስቆጪ ነው የሚሉት የቱሪዝም ኢኮኖሚ ባለሙያው ፍሬዘር አለሙ አሁንም የአዲስ አበባ ከንቲባ በዚህ ልክ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ማለታቸው ለመዲናዋም ሆነ ለሀገር ሁለንተናዊ ከፍታና ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

አትሌቶቻችን ሀገራቸውን በወከሉባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ለዚህ ሰንደቅ ዓላማ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ለሰንደቅ ዓላማው ያላቸውን ክብር በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር ገልጠዋል።

ለአፍሪካውያን አትሌቶች ፈር ቀዳጅ ከሆነው አትሌት አበበ ቢቂላ እስከ ማሞ ወልዴ፤ ከምሩፅ ይፍጠር እስከ ደራርቱ ቱሉ፤ ከኃይሌ ገብረሥላሴ እስከ ፋጡማ ሮባ፤ ከገዛኸኝ አበራ እስከ ቀነኒሳ በቀለ እና ስለሺ ስህን እንዲሁም ከመሠረት ደፋር እስከ ጥሩነሽ ዲባባ፣ . . እንቁ አትሌቶቻችን የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው አውለብልበዋል።

ይህንን ታላቅ ገድልና ድል ተገቢውን ክብር በመስጠት በስፖርት ቱሪዝም ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነትን የበለጠ ከፍ ባለ መልኩ መጠቀም እንደሚቻል አውስትራሊያን፣  ስፔንን፣ አሜሪካን እና ብራዚልን የመሳሰሉ ሀገራትን በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

በመለሰ ተሰጋ     

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review