የመዲናዋ ጥበባዊ መረጃዎች

You are currently viewing የመዲናዋ ጥበባዊ መረጃዎች

ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መሰናዶዎች ይቀርባሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የመጻህፍት ምረቃ፣ ጥበባዊ የሃሳብ ውይይት፣ የሥዕል አውደ ርዕይና የቴአትር መርሃ ግብር ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጻህፍት

ዛሬ ቅዳሜ ከ 10:00 ሰዓት ጀምሮ  የገጣሚ መንበረ ሐይሉ “የውበት ሰሌዳ” የተሰኘው የግጥም መድብል ፒያሳ በሚገኘው ጣይቱ የባሕልና የትምህርት ማዕከል ውስጥ ይመረቃል፡፡ በስነ ሥርዓቱ ላይ የተለያዩ ጥበባዊ መሰናዶዎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ታዋቂ የጥበብ ሰዎችም በመድረኩ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንድትገኙ  ሁላችሁንም  በክብር ተጋብዛችኋል፡፡

በተመሳሳይ መረጃ “መንፈሳዊ መነቃቃትን እውቀት መፈለጊያ ማድረግ” በሚል የፓናል ውይይት ይደረጋል፡፡ “ሰዎች እለት በእለት ከሕይወት መመሪያቸው ጋር እንዴት ተቆራኝተው  መጓዝ ይችላሉ?” የሚለውን መነሻ ሃሳብ መሰረት በማድረግ በሙያቸው የታወቁ  ተመራማሪዎች ርዕሰ-ጉዳዩን ያብራሩታል፡፡ ዛሬ ቅዳሜ ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ በሚደረገው በዚህ የፓናል ውይይት ላይ መነሻ ሃሳብ ከሚያቀርቡ ሰዎች መካከል መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል፣ ዑስታዝ አህመድ ሙስጠፋና መምህር አሌክስ ዘፀአት ይገኙበታል፡፡ የፓናል ውይይቱን የሚመራው ተመስገን ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ ውይይቱ ያሰናዳው ዋልያ የሃሳብ እና መጽሐፍ መድረክ ሲሆን፣ የሚካሄድበት ቦታ ደግሞ 4 ኪሎ ኢክላስ ህንፃ ዋልያ መጻሕፍት አዳራሽ ነው፡፡

ፊልም

አጫጭር ፊልሞች ላይ ያተኮረው ሙያዊ ውይይት ዛሬም ይቀጥላል፡፡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል አጫጭር ፊልሞች ላይ ያተኮረ ሙያዊ ውይይት ባለፉት ሁለት ቀናት ሲያካሄድ ቆይቷል። ውይይቱ ዛሬም የሚቀጥል ሲሆን፣  ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በአካዳሚው ቅጥር ግቢ ይካሄዳል፡፡ ከውይይቱ በፊት የተለያዩ አጫጭር ፊልሞች እንደሚቀርቡም ታውቋል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ በአንጋፋው የፊልም ባለሙያ ብርሃኑ ሽብሩ በሚቀርቡ አጫጭር ፊልሞች ላይ ሙያዊ ዳሰሳውን ያቀርባል፡፡ ዝግጅቱ የአለ ስነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት እና የልቀት ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች በሰሯቸው አጫጭር ፊልሞች ላይ ያተኩራል ተብሏል። ዝግጅቱ የሚካሄድበት ስፍራ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል ውስጥ ሲሆን፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ አካባቢ (በንግድ ባንክ ጉለሌ ቅርንጫፍ በኩል ገባ ብሎ) ይገኛል፡፡

ሥዕል

ከሳምንት በፊት በፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ በይፋ የተከፈተው ‘አብሮነት’ የሥዕል አውደ ርዕይ የተለያዩ የሥዕል ሥራዎች የቀረቡበት ነው ተብሏል። ሰዓሊያን በቡድን ሆነው ባሰናዱት በዚህ የሥዕል አውደ ርዕይ አብሮነትና ህብረትን የሚያሳዩ የሥዕል ስራዎች ቀርበዋል፡፡ በአውደ ርዕዩ ላይ የሥዕል ሥራዎቻቸውን ካቀረቡ ሰዓሊያን መካከል ብሩ ወርቁ፣ ያሬድ ወንድወሰንና ዘውዱ ገብረሚካኤል ይገኙበታል፡፡ አውደ ርዕዩ እስከ መጪው ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለተመልካች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

በተያያዘ መረጃ የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሥነ ጥበብ ትምህርት ክፍል ተመራቂ ተማሪዎች ያዘጋጁት የሥነ ጥበብ ዓውደ ርዕይ ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ ተከፍቷል፡፡ በሥዕል አውደ ርዕዩ የተለያዩ ጥበባዊ የስዕል ሥራዎች የቀረቡበት ነው ተብሏል፡፡ የሥዕል አውደ ርዕይዩ ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ እስከ ፊታችን ታህሣሥ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በኮሌጁ የሥዕል ማሳያ ውስጥ በእይታ ላይ ይቆያል ተብሏል።

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review