ልጆች፤ በሀገራችን ኢትዮጵያ ህዳር 29 የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በተለያዩ መርሃ ግብሮት ለ19 ጊዜያት ሲከበር ቆይቷል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ልጆች፤ በሀገራችን ኢትዮጵያ ህዳር 29 የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ለ19 ጊዜያት ሲከበር ቆይቷል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት አስተናጋጅነት ለ20ኛ ጊዜ በሆሳእና ከተማ “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በድምቀት ይከበራል፡፡
ልጆች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ምን ያህሎቻችሁ ታውቃላችሁ? በምን መልኩ ነው የምታከብሩት? መከበሩስ ምን አይነት ግንዛቤ አስጨብጧችኋል? የሚሉትን እና መሰል ጉዳዮች እርስ በእርስ ተነጋገሩባቸው፡፡ የዝግጅት ክፍሉ ደግሞ ካነጋገርናቸው ልጆች ያገኘውን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡
ናታሊም ዮናስ እባላለሁ። ህዳር 29 ምንም እንኳን የተለያየ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ብንሆንም በልዩነታችን ውስጥ ያለውን አንድነታችንን የምናሳይበት እለት ነው፡፡ በዕለቱ የራሴ መገለጫ የሆነውን የባህል ልብስ እለብሳለሁ፡፡ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይም ባህሌን አንጸባርቃለሁ፡፡ ልክ እንደ እኔ ሌሎች ጓደኞቼም እንደየብሔራቸው የባህል ልብስ ይለብሳሉ፡፡ በዚህም ስለተለያዩ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህል እንዳውቅ አድርጎኛል፡፡
ሳዶር ኤልያስ እባላለሁ፡፡ ህዳር 29 የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ሲከበር ልዩ ስሜትና ደስታ ይሰጠኛል፡፡ ምክንያቱም የብዙ ብሔሮች ብሔረሰቦችን እና ህዝቦችን ባህላዊ አልባሳት፣ የጸጉር አሰራር፣ አጨፋፈር አያለሁ፡፡ በእለቱ በትምህርት ቤትም ይሁን በቴሌቪዢን የተለያዩ አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራሞች ይቀርባሉ፡፡ እኔም ያለኝን ባህላዊ ልብስ ለብሼ እውላለሁ፡፡
የቀኑ መከበር ብዙ አይነት ባህሎች እንዳሉ እንድናውቅ ይረዳናል፡፡ በሌሎች ቀናት አንድ እና ሁለት ልናውቅ እንችላል፤ ቀኑ ሲከበር ግን በርካታ ባህሎችን እንድንረዳ ያደርጋል፡፡ በጋራ ስናከብር ስለማናውቃቸው ብሔሮችና ባህላቸው በአጠቃላይ ስለሀገራችን እንድናውቅ ያደርገናል፡፡
ጺዮን አየለ እባላለሁ፡፡ በሀገራችን ያሉ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ተዋደውና ተፋቅረው እየኖሩ ያሉ ናቸው፡፡ ሁላችንም የባህል ልብሶቻችንን ለብሰን የምንውልበት ቀን ነው፡፡ ጭፈራ ይጨፈራል፡፡ ሁላችንም የየራሳችን ባህል የምናስተዋውቅባቸውን አልባሳት፣ ጸጉር አሰራር የምናሳይበት ነው፡፡ እኔም በእለቱ የባህል ልብሴን ለብሼ እውላለሁ። በዚህም ባህሌን ሌሎች እንዲያውቁት አደርጋለሁ፡፡
ስሜ ተውሂዳ አብዱልአዚዝ ይባላል። ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን ባህል፣ ቋንቋ፣ የአመጋገብና አለባበስ ያላቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ ቀኑ በሀገራችን በየዓመቱ መከበሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መኖራቸውን እንዳውቅ አድርጎኛል። በተጨማሪም ሁሉም የየራሳቸው መገለጫ የሆነ ባህል፣ ወግ እና ቋንቋ ያላቸው መሆኑን አሳውቆኛል። በዓሉን ስናከብር ሁላችንም በልዩነት ውስጥ አንድ መሆናችንን በማድመቅ መሆን አለበት እላለሁ፡፡
በለይላ መሀመድ