• በመዲናዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ወደ ከባቢ የሚለቀቀውን ሙቀት አማቂ ጋዝ በመቀነስ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ተመላክቷል
የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ በተለይ አፍሪካ ዳፋው ብርቱ ክንዱን እያሳረፈባት ያለች አህጉር ናት፡፡ ኢትዮጵያ እንዲሁም መዲናችን አዲስ አበባም ከዚህ ተፅዕኖ የተላቀቁ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም ለዚህ መፍትሔ የሚሆኑ ስራዎችን በመስራት ለሌሎች ሀገራት ጭምር አርዓያ መሆን እየተቻለ ነው፡፡
በዛሬው አጭር ዳሰሳችን የሙቀት አማቂ ጋዝ ምንድ ነው? ተጽዕኖውስ? የሙቀት አማቂ ጋዝን ለመከላከል አዲስ አበባስ ምን እየሰራች ነው? የሚለውን ቃኝተናል፡፡
አቶ ሰለሞን መለሰ ይባላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአየር ንብረት ለውጥ አማራጭ ኢነርጂ ዳይሬክቶሬት የሙቀት አማቂ ጋዝ ልኬት ቅነሳና አረንጓዴ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያና የአየር ጥራት ክትትል ቡድን መሪ ናቸው።
የሙቀት አማቂ ጋዝ ምንነትን ሲገልጹ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ ዋና መንስኤ የሚሆነው የሙቀት አምጪ ወይንም የሙቀት አማቂ ጋዝ ወደ አየር መለቀቅ ክምችት መጨመር ነው፡፡ እነዚህ እንደ ሚቴን፣ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ፣ ናይትሮጂንዳይ ኦክሳይድ የሚባሉት አማቂ ጋዞች በተለያየ ምክንያት ወደ ከባቢ አየር ይለቀቃሉ፡፡
እንደ ቡድን መሪው ገለጻ፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ አማቂ ጋዞችን መጠን በየሁለት ዓመቱ ይለካል፤ ልኬቱንም ሪፖርት ያደርጋል። እስካሁንም ለ4ኛ ጊዜ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልኬት ተከናውኖ ሪፖርት ተደርጓል። በ2015/2016 ዓ.ም ለ4ኛ ጊዜ የተደረገው ሪፖርት 6 ሚሊዮን 953 ሺህ ቶን የሙቀት አማቂ ጋዝ ወደ ከባቢ መለቀቁን ያሳያል፡፡ በሴክተሮች የሚለቀቀውን የጋዝ መጠን ያሳያቸዋል፡፡ የሚለቁት የጋዝ መጠን እያደገ ከመጣ የአየር ንብረቱ እየተለወጠ ስለሚመጣ ከባቢው ለመኖር ምቹ አይሆንም፡፡
ዋና የሙቀት አማቂ ጋዝ አመንጪ ሴክተሮች
እንደ አቶ ሰሎሞን ገለጻ፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ ከተማ “ዋና የሙቀት አማቂ ጋዝ አመንጪ ናቸው” ብሎ ከለያቸው ሴክተሮች ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የትራንስፖርት ሴክተሩ ነው፡፡ ከአጠቃላይ 6 ቢሊየን 953 ሺህ ቶን ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ልቀት ውስጥ 5 መቶ ሚሊየን አካባቢው የሚመነጨው ከትራንስፖርት ነው፡፡ ትራንስፖርት ሲባል አቬሽን እና የመንገድ ትራንስፖርት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 2 ሚሊየን 508 ሺህ ቶን በመንገድ ላይ በትራንስፖርት የሚመጣ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት መጠን ነው፡፡ 2 ሚሊየን 503 ቶን የሚሆነው ደግሞ የአቬሽን ነው፡፡ በአቬሽን የሚለቀቀው አውሮፕላኖች 50 ኪሎ ሜትር ርቀው እስከሚሄዱ ድረስ የሚለቀቅ ነው፡፡
እንደ ከተማ ከፍተኛው አማቂ የጋዝ ልቀት የሚመነጨው ከመኪና ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ነው። ይህ ቆሻሻ 1 ሚሊየን 200 ሺህ አካባቢ የሙቀት አማቂ የጋዝ ልቀት ያደርጋል። ወደ ረጲ የሚጓጓዘው ደረቅ ቆሻሻ እንደ ሚቴን አይነት ከፍተኛ የሙቀት አማቂ ጋዝ ወደ አየር ይለቃል፡፡ ሌላው ወደ ማጣሪያ የሚሄዱ የፍሳሽ ቆሻሻዎችም ሚቴን ጋዝ ይለቃሉ፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የሙቀት አማቂ ጋዝ የሚለቀቀው ከኢነርጂ ሴክተር ነው፡፡ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች፣ እንጨት፣ ከሰል፣ ቡታጋዝ፣ ሲሊንደር ጋዝ የመሳሰሉት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት አማቂ ጋዝ አለ፡፡ በአራተኛ ደረጃ ኢንዱስትሪና ግብርና ናቸው፡፡ ኢንዱስትሪ ላይ ያለው የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ዝቅተኛ ነው። የግብርናው ሴክተር ኬሚካል ማዳበሪያ ስለሚጠቀም ከፍተኛ ሙቀት አማቂ ጋዝ ይለቃል፡፡ ሌላው ለከብቶች የተሻሻለ መኖ ስለማይዘጋጅ በሚያመነዢኩበት ወቅት እና በሚያስወግዱት ቆሻሻ ናይትሮጂን ዳይ ኦክሳይድና ሚቴን ጋዝ ወደ ከባቢ አየር ይለቀቃል፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሴክተሮች ከፍተኛ የሙቀት አማቂ ጋዝ አመንጪዎች ተብለው መለየታቸውን ቡድን መሪው ተናግረዋል፡፡
የሙቀት አማቂ ጋዝን መጨመር ተጽዕኖ
ደረጃውን ስናይ ለምሳሌ ባለፈው የትራንስፖርት ሴክተሩ ሲታይ እ.ኤ.አ ከ2012፣ 2016 እና 2023 እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም አሁንም ገና ይቀረዋል፡፡ ለዚህ ዋና ምክንያት የአሮጌ መኪና መስፋፋት ነው። የግል ተሽከርካሪዎች በተለይም የነዳጅ መኪናዎች ቁጥር መጨመር እና የመንገድ መሰረተ ልማት አለመስፋፋት ሌሎች ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው። መኪና በጨመረ ቁጥር መንገድ ክፍት ካልሆነ ተሽከርካሪዎች ነድጅ ስለሚያቃጥሉ ከፍተኛ ሙቀት አማቂ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር ይለቀቃል፡፡ ፈጣን የአውቶቡስ ትራንስፖርት አለመኖርና አለመስፋፋት ሌላው ምክንያት ነው፡፡ የመኪና ፍተሻ ላይ ትኩረት አለመስጠት። የተሽከርካሪዎችን አቅምና ብቃት በተገቢው መንገድ ሳይለካና ሳያረጋግጥ ቦሎ የመስጠት ችግር መኖር ነው፡፡
የሙቀት አማቂ ጋዝ እየጨመረ መምጣት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ሥነ ምህዳሩ እየተለወጠ የመምጣት ችግር ነው፡፡ በተለይም በረሀማነትን ያስፋፋል። ቀደም ሲል ደጋ የነበረው አካባቢ ወደ ወይናደጋነት፣ ወይናደጋ የነበረው አካባቢ ደግሞ ወደቆላማነት እየተለወጠ መጥቷል። በአሁኑ ወቅት ሙቀት እየጨመረ በመምጣቱ ደጋ ይበቅሉ የነበሩ የተክል አይነቶች እንዳይበቅሉ እያስገደዳቸው ነው። የአየር ንብረት ለውጡ የበለጠ እየተቀየረ ከሄደ እጽዋት ብቻ ሳይሆኑ ሰዎችን ጨምሮ ለሌሎች ህይወት ላላቸው ነገሮች ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ ስለሆነም ምቹ የአየር ንብረት ለውጥ ለመፍጠር የሙቀት አማቂ ጋዞችን መቀነስ አስፈላጊ ነው፡፡
መፍትሔው
ቡድን መሪው አያይዘውም፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የሙቀት አማቂ ጋዝ አምጪ የሆኑ ሴክተሮችንና ማህበረሰቡን ስለጉዳዩ ከማሳወቅና ከማስገንዘብ በተጨማሪ ምን መስራት እንዳለባቸው በተለይም ልቀቱን እንዲቀንሱ የሚያስችሏቸውን ስራዎች እቅድ ይዘው እንዲሰሩ የክትትልና ድጋፍ ስራ ይሰራል።
ከደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ጋር በተያያዘም የተሻለ ግንዛቤ ያለ ቢሆንም የበለጠ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ደረቅ ቆሻሻን አሁን እንደተጀመረው በመልሶ መጠቀም የተለያዩ ነገሮችን ማምረትና ለኮምፖስት አገልግሎት እንዲውል ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ፈሳሽ ቆሻሻን አጣርቶ ወደ ወንዝ ከመልቀቅና ለመጠጥ ከማዋል ለአረንጓዴ ልማት ማዋል፣ ዝቃጩንም ለአትክልት ማዳበሪያነት ከማዋል የተበላሸ መሬት ላይ በመድፋት መሬቱ እንዲያገግም በማድረግ ወደ ረጲ የሚጓጓዘውን ቆሻሻ መቀነስ ይገባል፡፡
ቡድን መሪው አያይዘው በሰጡት መረጃ፤ የፍሳሽ ቆሻሻ የሚፈጥረውን ሜቴን ጋዝ ወደ ሀይልነት መለወጥ ያስፈልጋል። ለምሳሌ በሀገራችን ኢነርጂ ላይ እ.ኤ.አ 2021 በኢነርጂ ይለቀቅ የነበረው አማቂ ጋዝ 803 ሺህ ቶን ነበር፡፡ እ.ኤ.አ 2023 ደግሞ 300 ሺህ ቶን ደርሷል፡፡ ይህም አሁን ላይ የተሻሻለ የኤሌክትሪክ ምድጃ መጠቀም ተጀምሯል ማለት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ የተሻሻለ ቢሆንም አሁንም በየቤቱ ከሰል የሚጠቀም የማህበረሰብ ክፍል አለ፡፡ ከሰል ብቻም ሳይሆን ቡታ ጋዝና ሲሊንደር ጋዝ በየቤቱ ግለሰቦች የሚጠቀሟቸው አማራጭ የሀይል አቅርቦቶች ናቸው፡፡
ትራንስፖርት ላይ የተሸከርካሪዎችን ብቃት በሚገባ በመመርመር አገልግሎታቸው ያለፈባቸውን በማስወጣትና ተለዋጭ መፍትሔ በመስጠት ችግሩን ማስወገድ ያስፈልጋል። በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርቶችን ከማመቻቸትም ባለፈ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መሸከም ስለሚችሉ ቁጥራቸውን መጨመር ይገባል፡፡ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ማስፋፋት እና የባቡር ትራንስፖርቶችን ማስፋትም ተገቢነት አለው፡፡
የግብርናው ሴክተር መሬታቸው ላይ ኬሚካል ማዳበሪያ ከሚጠቀሙ ኮምፖስት መጠቀም፣ ከብቶች በየቦታው የሚያስወግዱትን ቆሻሻ (እዳሪ) ሰብስቦ ወደ ባዮጋዝ መለወጥ፣ የከብቶችን የማመንዠክ መጠን ለመቀነስ ለከብቶቹ የተሻሻለ መኖ ማዘጋጀት ይገባል፡፡ አሁን ላይ አማቂ ጋዝ ክምችት መጠን ውስን መሻሻል ያለ ቢሆንም የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የሚመረቱ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2050 እንደ ሀገር ዜሮ ካርቦን ልቀት ማድረስ የሚል ግብ ተጥሎ ነው ጥረት እየተደረገ ያለው። በዚህም እያደገ የመጣውን የካርቦን ክምችት ለመቀነስ ብዙ መስራት ይጠይቃል፡፡ ብዙ ቴክኖሎጂ ማስፋፋት ያስፈልጋል። የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ትኩረትም ሙቀት አማቂ ጋዝ አምጪ ሴክተሮች የሚለቁትን መጠን እንዲቀንሱ ማስተባባርና አቅጣጫ ማሳየት ነው። በኮሪደር ልማቱ የተሰራው የእግረኛ መንገድና የብስክሌት መንገድ መስፋፋት፣ አንዳንድ ቀን አስፋልት መንገዶች ከተሽከርካሪ ነጻ እንዲሆኑ ማድረግ ወደ ከባቢ የሚለቀቀውን ጋዝ በመቀነስ ረገድ ጉልህ ሚና ስላለው እንዲህ አይነት እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡
በለይላ መሀመድ