የጨጓራ ካንሰር መንስኤ ምንድነዉ? ምልክቱና እና ህክምናውስ?

You are currently viewing የጨጓራ ካንሰር መንስኤ ምንድነዉ? ምልክቱና እና ህክምናውስ?
  • Post category:ጤና

AMN – ህዳር 13/2018 ዓ.ም

የጨጓራ ካንሰር ከፍተኛ እና ውስብስብ ጉዳት ከሚያስከትሉ የካንሰር ዓይነቶች የሚመደብ ነው፡፡

የጨጓራ በሽታ የሚጀምረው በጨጓራ የውስጠኛው ክፍል ሲሆን፣ ህመሙ ቀስ በቀስ ወደ ጨጓራ ግድግዳ በመሄድ ቁስለትን በመፍጠር የካንሰር ቫይረስ እንዲራባና እንዲሰራጭ ያደርጋል፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የካንሰር ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ሙሉጌታ ካሳሁን ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ የጨጓራ ካንሰር በሽታ በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚከሰት በሽታ ሲሆን፤ በአብዛኛው ግን ከ60 እና ከ70 ዓመት ዕድሜ የሚገኙ ሰዎችን እንደሚያጠቃ ገልፀዋል፡፡

የጨጓራ ካንሰር በሽታ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፤ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ከደረሰ በኋላ አክሞ ለመዳን ውስብስብ በመሆኑ፣ በሽታው ሥር ሳይሰድ መታከም እንደሚገባ ዶ/ር ሙሉጌታ ይመክራሉ፡፡

ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የጨጓራ ቁስለት፣ በአካባቢ ንጽሕና ጉድለት የሚከሰት የጨጓራ ቫክቴሪያ፣ የተጠበሱ እና ጨዋማ ምግቦችን መመገብ ለጨጓራ ካንሰር በሽታ መንስኤ ናቸው፡፡

ከእምብርት በላይ ህመም፣ የምግብ አለመፈጨት፣ የምግብ ፍላጐት መቀነስ፣ ማቅለሽለሽ፣ የሰውነት ክብድት መቀነስ፣ ደም ማስመለስ፣ የሆድ ህመም እና የጀርባ ህመም የበሽታው ምልክቶች ናቸው፡፡

እነዚህ ምልክቶች ከታዩ በኋላ በኢንዶስኮፒ፣ በአልትራሳውንድ፣ በላብራቶሪይ፣ በሲቲ ስካን የበሽታው የጨጓራ ካንሰር መሆኑን ማረጋገጥ ይችላል፡፡

የጨጓራ ካንሰር መሆኑ ከተረጋገጠ እንደ ካንሰሩ ደረጃ በሚዋጥ መድሃኒት፣ በጨረር እና በቀዶ ህክምና በሽታውን ማከም እንደሚቻል ዶ/ር ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡

የታሸጉ ምግቦች ባለመመገብ፣ ሲጃራ ባለማጨስ፣ አልኮል መጠጥ ባለመጠጣት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ፣ አትክልትና ፍራፍሬ መመገብ በሽታውን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነ ዶ/ር ሙሉጌታ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፤

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review