ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ወደ አካታች ዕድገት እየተጓዘች መሆኗን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ በሚገኘዉ የቡድን 20 ሀገራት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ከመሆኗም ባሻገር አሁንም መድረሻዋን ተልማ አዲስ ታሪክ እየተጻፈ ያለች ሀገር መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶችን በውስጧ አቅፋ የያዘች የብዝሃነት ተምሳሌት መሆኗን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሕዝቦቿ ትስስርም ዘላቂነት ባለዉ የማህበረሰብ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በልዩነት ውስጥ አንድነትንና አቅምን የሚያበዛ : የትብብር : የቅንጅት እና ለሁሉም የሚጋራ የዕድገት ፍልስፍና ውርስ የሆነው የመደመር ዉጤት ነዉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ የመደመር መንፈስ እየተመራች ወደ አካታች ዕድገት እየተጓዘች መሆኗን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ከተሞች የፈጠራ ማዕከላት እየሆኑ መምጣታቸውን ጭምር አንስተዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢኮኖሚዎችን እየቀየሩ መሆናቸዉን: አርሶና አርብቶ አደሮች ወላጆቻቸው ፈጽሞ ሊያስቡት የማይችሉትን የግብርና መሣሪያዎችን እና ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀሙ መሆኑን አንስተዋል።
ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ከአንድ ትውልድ በፊት ለመመኘት የሚያስቸግሩ ግዙፍ የንግድ ሥራዎችን እየከፈቱላቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመላክተዋል።
እንደኛ ያሉ ሃገራት ለረጅም ጊዜያት “ደካማ” ወይም “ድሃ” ተብለው ሲፈረጁ ነበር : አሁን ላይ ግን ታሪካችን በሰላማዊ አብዮት ላይ ይገኛል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸዉ።
ዕድገት ወደ ኋላ መቅረትን እምቢ በሚሉ ሰዎች የሚመዘገብ ስኬት ነዉ ያሉት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር) ታሪካችንን እንደገና ለመጻፍ በሚቻለን አቅም ሁሉ ጠንካራ አብዮት በማከናወን ላይ እንገኛለን ብለዋል።