ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መለኪያዎችን መሠረታዊ በሆነ መንገድ እንደገና ለማዋቀር የሚጠይቅ አዲስ የፖሊሲ ሀሳብ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በተጀመረው የቡድን ሃያ ሀገራት (G20) የመሪዎች ጉባኤ ላይ ቀርቧል።
በጉባኤው ላይ ሀሳባቸውን ያካፈሉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እስከዛሬ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርትን (GDP) ብቻ የዕድገት መለኪያ ከማድረግ የሚያወጣን አዲስ ዕይታ ሊኖረን ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት የአንድ ማሕበረሰብ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ጫናን ተቋቋሞ መቆየት እና ከሁኔታዎች ጋር ራስን አስማምቶ የመቀጠል አቅም ዘላቂ ልማትን እንደማስመዝገብ ሊቆጠር ይገባዋል።
ይህ “አይበገሬነትን እንደ እድገት” መለኪያ የመውሰድ ሀሳብ ከመደመር መሠረታዊ ዕሳቤ የመነጨ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልጸው ዓለም አቀፋዊ ለሆነው የጋራ ዕድገት ኢትዮጵያ የራሷን አስተዋጽዖ ለማበርከት ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
ለ2 ቀናት የሚካሄደው የቡድን 20 ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ሕዳር 14/2018 ድረስ ይቆያል።