አርሰናል መሪነቱን ለማጠናከር በሰሜን ለንደን ደርቢ ቶተንሃምን ይገጥማል

You are currently viewing አርሰናል መሪነቱን ለማጠናከር በሰሜን ለንደን ደርቢ ቶተንሃምን ይገጥማል

AMN-ህዳር 14/2018 ዓ.ም

የ12ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂ ጨዋታ በአርሰናል እና ቶተንሃም ሆትስፐርስ መካከል ይደረጋል።

አርሰናል የሊጉ ሂደትን በራሱ ቁጥጥር ስር አድርጎ ለማስቀጠል ሦስት ነጥቡ ያስፈልገዋል።

መድፈኞቹ በተለይ የማንችስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል መሸነፍ የበለጠ ተነሳሽነት ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የሚካኤል አርቴታው ቡድን ከሀገራት የዓለም አቀፍ ጨዋታዎች በፊት ከሰንደርላንድ አቻ ቢወጣም እስካሁን ያሳየው ብቃት ደጋፊዎቹ ተስፋ እንዲያደርጉ ያስቻለ ነው።

ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድኑ ጋብሬኤል ማጋሌሄስን በጉዳት ማጣቱ መጠነኛ ስጋት ፈጥሯል።

ለዚህ ጊዜ የተዘጋጀ የሚመስለው ሚካኤል አርቴታ የተከላካይ አማራጩ ሰፊ ነው።

ብራዚላዊውን ተከላካይ የሚተካው ተጫዋች በእርሱ ልክ ተፅዕኖ ይፈጥራል ወይ የሚለው ግን ትልቅ ጥያቄ ይሆናል።

በዛሬው ጨዋታ የቪክቶር ዮኬሬሽ እና ጋብርኤል ማርቲኔሊ መግባት አልተረጋገጠም።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከሜዳው ውጪ የተለየ ቡድን ነው። ካደረጋቸው አምስት ጨዋታ አራቱን አሸንፎ አንዱን አቻ ተለያይቷል።

በቶማስ ፍራንክ የሚመራው ቶተንሃም ከሜዳው ውጪ ሽንፈት ያልገጠመው የሊጉ ብቸኛው ቡድን ነው።

የሚገርመው ግን ቶተንሃም በሜዳው ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ነው በድል የተወጣው።

ቶተንሃም በሰሜን ለንደን ደርቢ ያለው ክብረወሰን ደካማ እንደሆነ የኦፕታ ቁጥራዊ መረጃ ያሳያል።

በተለይ ወደ አርሰናል ሜዳ ተጉዞው የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በሽንፈት ታጅበው ነው የሚጠናቀቁት።

አርሰናል በሜዳው ቶተንሃምን ባስተናገደበት 32 የመጨረሻ ጨዋታ የተሸነፈው በአንዱ ብቻ ነው። 19ኙን አሸንፏል።

በኤምሬትስ የሚከናወነው የዛሬው 212ኛው የሰሜን ለንደን ደርቢ ጨዋታ ምሽት 1:30 ላይ ይጀምራል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review