የልብ እና የደም ቧንቧዎች በተለያዩ በሽታዎች የሚጠቁ ሲሆን፣ መንስኤያቸውም የተለያየ እንደሆነ የዘርፉ ባለሞያዎች ይናገራሉ።
በደም ቧንቧዎች የውስጠኛው ግርግዳ ላይ አላስፈላጊ የስብ ክምችት ሲኖር የደም ቧንቧዎች ተፈጥሯዊ ቅርፃቸውን ስለሚያጡ በቂ ደም ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ለማድረስ መቸገር የልብ እና የደም ቧንቧ በሽታን ያመላክታል።
በስብ ክምችት የሚከሰተው በሽታ የልብ እና የደም ቧንቧ እንደሚገኝበት ቦታ እና አይነትም ይለያያል።
የስብ ክምችት ደምን ከልብ ወደ አዕምሮ በሚወስዱ የደም ቧንቧዎች የውስጥ ግድግዳ ላይ በመጣበቅ በቂ ደም ወደ አዕምሮ የማይሄድ ከሆነ የአእምሮ ክፍል ላይ ደም ማጣት ሊያስከትል ይችላል።

ሲጋራ ማጨስ፣ የሰውነት ክብደት መጨመር፣ የደም ግፊት በሽታ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የስኳር ህመም፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ እድሜ እና የዘር ሀረግ በልብ እና በደም ቧንቧ በሽታ የመያዝ እድል የሚጨምሩ መንስኤዎች ናቸው፡፡
አብዛኛውን ጊዜ የልብ እና የደም ቧንቧ በሽታዎች ምንም አይነት ምልክት አያሳይም። ሆኖም ግን አንዳንዴ የደረት መውጋት፣ የድካም ስሜት፣ የትንፋሽ ማጠር፣ የሰውነት አካል በከፊል መስነፍ የልብ እና የደም ቧንቧ በሽታ ምልክቶች መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ለልብ እና ለደም ቧንቧ በሽታ እንድንጋለጥ የሚያደርጉ አብዛኛውን ሁኔታዎች በመከላከል ለበሽታው የመጋለጥ እድልን በቀላሉ መቀነስ ይቻላል

ከሲጋራ ማጨስ መቆጠብ ወይም ከሚያጨሱ ሰዎች መራቅ ፣ አከላዊ እንቅስቃሴ ማዘውተር ፣ የምንጠቀመውን የጨው መጠን መቀነስ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ማዘውተር እንደሚገባ ባለሞያዎች ይመክራሉ።
ከዚህ በተጨማሪ የሰውነት ክብደት እንዳይጨምር መቆጣጠር፣ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ፣ ስብ እና ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን አዘውትሮ ከመጠቀም መቆጠብ፣ ከልክ ያለፈ የአልኮል አጠቃቀምን ማስወገድ ይገባል
በየጊዜው የስኳር መጠን፣ የደም ግፊት እና የኮሊስትሮል እና ሌሎችንም የጤና ምርመራዎችን ማድረግ ያስፈልጋል።
የስኳር ወይንም የደም ግፊት ህመም ካለብዎት የህክመና ክትትልዎትን በአግባቡ መፈፀም የሀኪም ምክር በትክክል በመተግበር ይገባል።
መረጃው የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ነው።
በሔለን ተስፋዬ