በቡድን በመደራጀት በተለምዶ ሿሿ ተብሎ የሚጠራውን ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ እና ከወንጀለኞች የተሰረቀ እቃ የሚገዙ 36 ግለሰቦች እና 5 ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

You are currently viewing በቡድን በመደራጀት በተለምዶ ሿሿ ተብሎ የሚጠራውን ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ እና ከወንጀለኞች የተሰረቀ እቃ የሚገዙ 36 ግለሰቦች እና 5 ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN ህዳር 15/2018 ዓ.ም

በቡድን በመደራጀት በመዲናዋ በተለምዶ ሿሿ ተብሎ የሚጠራውን ወንጀል የሚፈፅሙ እና ከወንጀለኞቹ የተሰረቀ እቃን የሚገዙ ወንጀል ፈፃሚዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታዉቋል፡፡

ከወንጀሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው 36 ግለሰቦች እና 5 ተሽከርካሪዎች መያዛቸዉን ፖሊስ ገልጿል፡፡

ወንጀል ፈፃሚዎቹ ተሽከርካሪ ይዘው በመንቀሳቀስ እና ግለሰቦችን በማስፈራራት ስልክ የመቀማትና መሰል ድረጊቶችን ሲፈጽሙ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

በተሽከርካሪ እየተዟዟሩ ከወንጀል ፈፃሚዎች የተሰረቀ እቃ ሲገዙ የነበሩ ግለሰቦችም በህግ አግባብ በተደረገ ብርበራ እና ፍተሻ ከግለሰቦቹ መኖሪያ ቤት 30ሺ 700 ብር፣ 1 ላፕቶፕ፣ 1 ታብሌት፣ 11 ዘመናዊ ስልኮች፣ ተሰርቀው ቀፎዎቹ የተሸጡበት 188 የስልክ ከቨሮች በኤግዚቢትነት መያዙን የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡

በአጠቃላይ ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ 36 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑንም ፖሊስ መምሪያው ገልጿል።

በተለይም የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም የሚፈፀሙ የሿሿ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት ተባባሪ መሆን እንደሚገባው ያሳሰበው ፖሊስ ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አሳስቧል።

በወንጀሉ የምርመራ ሂደት አንዳንድ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ሆን ብለው ተሽከርካሪዎቻቸውን ለወንጀል ፈጻሚዎች እንደሚያከራዩ በምርመራ ተደርሶበታል፡፡

ድርጊቱ በግለሰቦቹ ላይ የሚያስከተለው የህግ ተጠያቂነት እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ፊት የተሽከርካሪያቸውን አይነትና የባለ ንብረቶቹን ስም ዝርዝር ለህዝብ ግልፅ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review