አዲስ ለተወለዱ ሕፃናት የሚሰጠውን የጉበት በሽታ መከላከያ ክትባት በሀገር አቀፍ ደረጃ
የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በአበበች ጎበና ሆስፒታል ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ የጉበት በሽታ በሀገሪቱ ከፍተኛ የጤና ችግሮች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጤናማ ማኅበረሰብን ለመፍጠር እየተደረገ ላለው ጥረት የዚህ የተጠናና ውጤታማ ክትባት መጀመር ወሳኝ ነው ብለዋል።
ማኅበረሰቡ የክትባቱ ተጠቃሚ እንዲሆን፣ በተለይም እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ በማሳሰብ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
አዲሱ የጉበት መከላከያ ክትባት ሕፃናት ከተወለዱ በ24 ሰዓታት ውስጥ የሚሰጥ ነው።
ይህ ክትባት ከተጀመረ በኋላም፣ ሕፃናት ሌሎች ክትባቶች እንደ ዕድሜያቸው መውሰድ የሚቀጥሉ ሲሆን፣የፔንታቫለንት (ፀረ አምስት) ክትባትም ሕፃናት በ6ኛ፣ በ10ኛ እና በ14ኛ ሳምንት ዕድሜያቸው ይሰጣቸዋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው፣ የጉበት በሽታ ከሚተላለፍባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዱ ከእናት ወደ ልጅ መሆኑን አረጋግጠው፣ ሕፃናትን እንደተወለዱ ወዲያውኑ ክትባቱን እንዲወስዱ ማድረግ ዋነኛ የመከላከያ መንገድ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአበበች ጎበና ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ዱሬቲ ጀማል እንደገለጹት፣ ይህ ክትባት በሽታው ከእናት ወደ ልጅ በወሊድ ጊዜ የሚተላለፈውን መንገድ በመዝጋት ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
በፅዮን ማሞ