በመዲናዋ ባለፉት አራት ወራት ከ5 ሺህ በላይ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ የደረሰኝ ቁጥጥር ተካሂዷል

You are currently viewing በመዲናዋ ባለፉት አራት ወራት ከ5 ሺህ በላይ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ የደረሰኝ ቁጥጥር ተካሂዷል

AMN-ህዳር 17/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት በ5 ሺህ 203 የደረቅ ጭነት ተሸከርካሪዎች ላይ የደረሰኝ ቁጥጥር አካሂዷል፡፡

የደረሰኝ ቁጥጥሩ የተካሄደው በሁሉም የከተማዋ አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ በሚገቡ፣ከከተማዋ በሚወጡና በከተማዋ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ፣ሚኒባሶችና አነስተኛ ሽፍን መኪኖች ላይ ነው፡፡

በዚህም ያለደረሰኝ ጭነት በመያዝ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 907 የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር የዋሉ ሲሆን 1 ሺህ 39 ግብር ከፋዮች ደረሰኝ እንዲቆርጡ 997 ግብር ከፋዮች ላይ ደግሞ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ መደረጉን የቢሮው ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በተደረገው የቁጥጥር ስራም የደረቅ ጭነት ተሸከርካሪዎቹ የጫኗቸው ሸቀጦች ላይ የ954 ሚሊዮን 803 ሺህ ብር ደረሰኝ እንዲቆረጥባቸው መደረጉንም ነው ኃላፊው የገለፁት።

በአሁኑ ወቅትም የደረሰኝ ቁጥጥሩ በቀን ብቻም ሳይሆን በለሊት ጭምር ተጠናክሮ መቀጠሉ የተገለፀ ሲሆን ደረሰኝ ሳይዙ ሸቀጦች በመጫን በሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች ላይ ከሚወሰድ አስተዳደራዊ እርምጃ በተጨማሪ በቀጣይ የደረቅ ጭነት አሽከርካሪዎቻቸው ላይም የህግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሚደረግ መሆኑንም አቶ ሰውነት ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review