የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ስለጋብቻ ምን ይላል
በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት እና በአዲሱ የቤተሰብ ህግ በህጋዊ እና አብሮ በመኖር የተፈፀመ ጋብቻ እውቅናና ከለላ የተሰጠው መሆኑን በየካ ክፍለ ከተማ ፍትህ ጽ/ቤት አቃቤ ህግ የሆኑት አቶ ማርቆስ ተስፋ ተናግረዋል፡፡
በሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት፣ በሀይማኖታዊ እና በባህላዊ ሥነ-ሥርአት የሚደረግ ጋብቻ በህግ የፀና ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ጋብቻ መኖሩን ለማረጋገጥ ተጋቢዎች የጋብቻ የምስክር ወረቀት ማስረጃ ሊኖራቸው ይገባል ያሉት አቃቢ ህጉ፡ በባህላዊ፣ በሃይማኖት እና በክብር መዝገብ ሹም የተገኘ ማስረጃ ህጋዊ እውቅና እንደሚኖረውም ገልፀዋል፡፡
በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 75 እና 76 መሠረት ጋብቻ የሚፈርስበት ሁኔታ መደንገጉን አቃቢ ህጉ ገልፀዋል፡፡
በህጋዊ ከተጋቡ ተጋቢዎች አንዱ በሞት እና ከአካባቢው መሰወሩ ወይም መጥፋቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ፣ ያለዕድሜ የተፈፀመ ጋብቻ ከሆነ እና ፍርድ ቤት በሚያፀናው ፍች መሠረት ጋብቻ ሊፈርስ እንደሚችል ተናግረዋል ፡፡
ለረጅም ጊዜ በፍቃዳቸው ተለያይተው መኖር የጋብቻ ፍች ፈጽመዋል ለማለት እንደማይቻል አመላክተዋል፡፡
በህጋዊ መንገድ የሚፈፀም ጋብቻ መብትና ግዴታን፤ የጋራና የግል ንብረት፣ የጋራ ወጪዎችን እና ልጆችን በተመለከተ በወረቀት በተዘጋጀ ውል ይፈራረማሉ፤ አብሮ በመኖር በሚፈፀም ጋብቻ ግን እነኚህ መስፈርቶ አይኖሩትም ሲሉ ነው ባለሞያው የገለፁት ፡፡
በህጋዊ መንገድ የተፈፀመ ጋብቻ በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 9 ላይ በተደነገገው መሠረት የጋብቻ ዝምድና የሚፈጠር በመሆኑ ቤተሰቦቻቸው በጋብቻ ሊተሳሰሩ እንደማይችሉ መደንገጉን አብራርተዋል ፡፡
በተመሣሣይም ከፍች በኃላ ቀለብ የመቁረጥ፣ ንብረት የመካፈል እና የልጆችን የኑሮ ሁኔታ የመወሰን ግዴታቸው እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡
በህግ አግባብ የተደረገ ጋብቻ ሳይኖር በመተባበር፣ በመተጋገዝ እና በፍቅር አንድ ጣሪያ ውስጥ በጋራ የሚኖሩ ጥንዶች በአዲሱ የቤተሰብ ህግ ጋብቻ እንደፈፀሙ ተደርጐ እንደሚቆጠር ገልፀዋል ፡፡
አብሮ በመኖር የሚፈፀም ጋብቻ ማስረጃ ወይም የምስክር ወረቀት የለውም ያሉት ባለሞያው ፍቺ ለመፈፀም ፍርድ ቤት መሄድም እንደማይጠበቅባቸውና በፈለጉት ጊዜ ግንኙነቱን በማቋረጥ ፍች መፈፀም እንደሚችሉ ነው የገለፁት ፡፡
በበረከት ጌታቸው