ህዳር 18/2018 ዓ.ም
ክልሎች በራሳቸው ጉዳይ በነጻነት እንዲወስኑ የተደረገው ከለዉጡ በኋላ ነዉ ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ተሬቻ ባልቻ ገለጹ፡፡
ተሬቻ ባልቻ የዘንድሮዉን የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከኤ ኤም ኤን ፕላስ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ የለዉጡ መንግስት ወደ አመራርነት ከመጣ በኋላ የሃገሪቱ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸዉን በራሳቸዉ የማስተዳደር ነጻነት እንደተጎናጸፉ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የክልል መንግስታት ሃገራዊ አንድነትን በጠበቀና ባከበረ መንገድ ያለምንም ጣልቃ ገብነት ራሳቸዉን በራሳቸዉ በማስተዳደር ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ሀገሪቱ ያለፉትን 30 ዓመታት የፌደራሊዝም ሥርዓትን በመተግበር ሂደትና ልምምድ ላይ የቆየች ቢሆንም በአተገባበሩ ላይ ትላልቅ ተግዳሮቶች እንደነበሩት ተሬቻ ባልቻ ለኤ ኤም ኤን ፕላስ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በህገ መንግስቱ የተጎናጸፉት መብት ቢኖርም አግባብነት በሌለዉ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ በመሞከሩ ሃገራዊ አንድነት እየተዘነጋ መሄዱን አስታውሰዋል፡፡
በወቅቱ ሲተገበር የነበረዉ የፌደራላዊ ስርዓት የተቋማትን ዴሞክራሲያዊነት ያከበረ ካለመሆኑም በላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አልነበሩም፡፡
የለዉጡ መንግስት ወደ አመራርነት ከመጣ በኋላ ግን የነበሩትን የፖለቲካ ልዩነቶች በመደመር እሳቤ እና በሰለጠነ የፖለቲካ አካሄድ መምራት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህግና ሥርዓትን መሰረት ባደረገ መንገድ በመከባበር፤ በመቻቻልና በመፋቀር ህብረ ብሔራዊ አንድነቱን ጠብቆ የሚኖር ህዝብ ነውም ብለዋል፡፡

ህገ መንግስቱ የጸደቀበት ህዳር 29 መከበር ከጀመረ 20 ዓመት ማስቆጠሩን የተናገሩት ተሬቻ ባልቻ፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በየአመቱ መከበሩ ወንድማማችነትን እና አብሮነትን ከማጠናከር ረገድ ትልቅ አርክቶ እንዳለዉ ተናግረዋል፡፡
አብሮ የመኖር ባህላዊ እሴቶችን ጨምሮ ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ለልማትና እድገት በጋራ መስራት እንደሚገባም አቶ ተሬሳ ገልጸዋል፡፡
በበየነ ታደሰ