ክልሎች በራሳቸዉ ጉዳይ በነጻነት እንዲወስኑ የተደረገዉ ከለዉጡ በኋላ ነዉ ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ተሬቻ ባልቻ ገለጹ፡፡
ተሬቻ ባልቻ የዘንድሮዉን የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከኤኤምኤን ፕላስ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፣ የለዉጡ መንግስት ወደ አመራርነት ከመጣ በኋላ የሃገሪቱ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸዉን በራሳቸዉ የማስተዳደር ነጻነት እንደተጎናጸፉ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የክልል መንግስታት ሃገራዊ አንድነትን በጠበቀና ባከበረ መንገድ ያለምንም ጣልቃ ገብነት ራሳቸዉን በራሳቸዉ በማስተዳደር ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

ሃገሪቱ ያለፉትን 30 ዓመታት የፌደራሊዝም ሥርዓትን በመተግበር ሂደትና ልምምድ ላይ የቆየች ቢሆንም፣ በአተገባበሩ ላይ ትላልቅ ተግዳሮቶች እንደነበሩት ተሬቻ ባልቻ ለኤኤምኤን ፕላስ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በህገ መንግስቱ የተጎናጸፉት መብት ቢኖርም የተሰጠዉን መብት አግባብነት በሌለዉ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ በመሞከር ሃገራዊ አንድነት እየተዘነጋ መሄዱን ጠቁመዋል፡፡
በወቅቱ ሲተገበር የነበረዉ የፌደራላዊ ስርዓት የተቋማትን ዴሞክራሲያዊነት ያከበረ ካለመሆኑም በላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አልነበሩም፡፡
የለዉጡ መንግስት ወደ አመራርነት ከመጣ በኋላ ግን የነበሩትን የፖለቲካ ልዩነቶች በመደመር እሳቤ እና በሰለጠነ የፖለቲካ አካሄድ መምራት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ህግና ሥርዓትን መሰረት ባደረገ መንገድ በመከባበር፤ በመቻቻልና በመፋቀር ህብረ ብሄራዊ አንድነቱን ጠብቆ የሚኖር ህዝብ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ህገ መንግስቱ የጸደቀበት ህዳር 29 መከበር ከጀመረ 20 ዓመት ማስቆጠሩን የተናገሩት ተሬቻ ባልቻ፣ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በየዓመቱ መከበሩ ወንድማማችነትን እና አብሮነትን ከማጠናከር ረገድ ትልቅ አርክቶ እንዳለዉ ተናግረዋል፡፡
አብሮ የመኖር ባህላዊ እሴቶችን ጨምሮ ሃገራዊ አንድነትን በማጠናከር ለሃገራዊ ልማትና እድገት በጋራ መስራት እንደሚገባም አቶ ተሬሳ ገልጸዋል፡፡
በበየነ ታደሰ