በማያቋርጥ መፍጠር እና መፍጠን መርህ እየሰራን የኢትዮጵያን ብልፅግና እናረጋግጣለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

You are currently viewing በማያቋርጥ መፍጠር እና መፍጠን መርህ እየሰራን የኢትዮጵያን ብልፅግና እናረጋግጣለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

AMN -ህዳር 18/2018 ዓ.ም

የብልፅግና ፓርቲ “በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ ሲሰጠው የቆየውን ስልጠና መጠናቀቅ ተከትሎ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችም የማጠቃለያ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማያቋርጥ “መፍጠር እና መፍጠን “ መርህ እየሰራን የኢትዮጵያን ብልፅግና እናረጋግጣለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየውን ሁለተኛ ዙር የስልጠና መድረክ ላይ ተገኝተው የማጠቃላያ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም አመራሩ በሁሉም መስኮች በስልጠናው ያገኘውን ግንዛቤ በተጨባጭ በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠልና ተግዳሮቶችን ወደ ድል በመቀየር፣ የተሻለችና የብልፅግና ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት ትኩረት ሊያደርግባቸው እንደሚገባ ተናግረዋል። በተቀመጡ የግብርና እና ገጠር ትራንስፎርሜሽን፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ እንዲሁም የቱሪዝምና ከተማ ልማት ዘርፍ እምርታን ለማስመዝገብ መግባባት የተፈጠረበት መሆኑንም ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።

የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች በበኩላቸው፣ በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል እና የተሻለ ዕድገት ለማምጣት አመራሩ በላቀ ትጋት መስራት አለበት ብለዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ርዕሳነ መስተዳድሮች በሰጡት አቅጣጫ የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ህብረተሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ አመራሩ ተቀናጅቶ መስራት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ አመራሩ ከተለመደው የአሰራር ስርዓት ተላቅቆ በመደመር መንግሥት እሳቤ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን ከዳር ለማድረስ በመፍጠርና መፍጠን ሊመራ ይገባል ብለዋል።

አቶ ሽመልስ አክለውም፣ በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በኢንዱስትሪ እድገት፣ በከተሞች ልማት እና በቱሪዝም ዘርፎች የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው፤ በስልጠና የተገኘውን ዕውቀት ወደ ተግባር መቀየር ከተቻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል። ለልማት እና ለመልካም አስተዳደር የተመቸ የፖለቲካ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አቶ አረጋ አስረድተዋል። የጸጥታ ኃይሉን ማጠናከር እና በመገንባት የኢኮኖሚ ልማት ሥራዎችን በውጤታማነት መምራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በከተማ ልማት ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ እንደሆኑ ገልጸዋል። በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠልና የተሻለ እድገት ለመፍጠር አመራሩ በላቀ ትጋት መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር፣ በግብርና ዘርፍ የተጀመሩ የተፋሰስ ልማት፣ የሌማት ቱሩፋት፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች እንዲሁም የመስኖ ልማት ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። ከተለመደው የአሰራር ስርዓት በመውጣት ምርታማነትን ለማሳደግ አዳዲስ አሰራሮችን በመጠቀም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባልም ብለዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ መሀመድም፤ የስልጠናው ተሳታፊ የነበሩ አመራሮች የወሰዱትን ትምህርት በሥራ ላይ እንዲያውሉ እና የመሪነት ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል። በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠልና የተሻለ ዕድገት ለመፍጠር አመራሮች በላቀ ትጋት መስራት አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፤ በብዝሃ ዘርፍ ላይ እመርታዊ ለውጥ በማስመዝግብ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እንዳሉት፤ የተጀመረውን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ ዕዉን ለማድረግ በከፍተኛ ትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡

ሰልጣኞች በስልጠናው ያገኙትን የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ዕዉቀት ከየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር በሁሉም ዘርፎች እመርታ ለማስመዝገብ መትጋት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፣ በስልጠናው በክልሉ በየዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጠናከር ሁለንተናዊ ብልፅግናን በማረጋገጥ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማስፋት ለተጀመረው ጉዞ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፣ የብልፅግና ፓርቲ እሳቤን ወደ ታለመለት ግብ ለማድረስ የአመራሩን አቅም መገንባት የሚኖረው ድርሻ የላቀ ነው ብለዋል።

ክልሉን የብልፅግና ተሞክሮ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ የፕሮጀክቶች የመፈፀም አቅምና የስራ ባህል ለውጥ የመጣበት መሆኑን ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፣ አመራሩ በስልጠናው ያገኘውን የንድፈ ሀሳብ ዕውቀትን ከተግባር ልምድ ጋር በማስተሳሰር የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በመፍጠር፣ሁሉአቀፍ አመራር በመስጠት የተጀመረዉን ክልላዊና ሃገራዊ ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በከፍተኛ ተነሳሽነትና በላቀ ቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡

ስልጠናው የአመራሩን የመፈፀምና የማስፈፀም ብቃት በማሳደግ የተጀመሩ ለውጦችን ቀጣይነት ያረጋግጣል ያሉት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ናቸው፡፡

በተለያዩ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ሲሰጥ የቆየው 2ኛው ዙር የበልፅግና ፓርቲ መካካለኛና ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ተጠናቋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review