የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከሞተር ሳይክል ማህበር አባላት ጋር ወንጀል መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ ለሁለተኛ ዙር ውይይት አካሃዷል።
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደንድር የአዲስ አበባ ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በሞተር ሳይክል የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል በትብብር እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ምክትል ኃላፊው ወንጀል ፈፅመው በተገኙት ላይም ርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።
በቀጣይም የከተማዋን ሰላም ለማደናቀፍ በሚሰሩት ላይም የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሞተር ሳይክሎችን ለስራ ብቻ በማዋል በሞተር ሳይክል የሚፈፀሙ ወንጀሎችን መከላከል እንደሚገባም አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በትብብር መመካከርና መወያየት አስፈላጊ በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረጉ ውይይቶች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመላክቷል።
በፅዮን ማሞ