የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለውጥ ለማፋጠንና ከፍተኛ የግል ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ቀጣናዊ ትብብር ወሳኝ ሚና እንዳለው አስገነዘቡ።
ኢትዮጵያ የተሳተፈችበትና በሞሮኮ ራባት ከተማ በተካሄደው የ2025 የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም አካል በሆነውና ምቹ በሆኑ አካባቢዎች የግል ኢንቨስትመንትን ማፋጠን በሚል ርዕስ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ንግግር አድርገዋል።
በዚሁ ወቅትም የአፍሪካን የኢኮኖሚ ለውጥ ለማፋጠንና ከፍተኛ የግል ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ቀጣናዊ ትብብር ያለውን ወሳኝ ሚና በአጽንኦት አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በጋራ ለመልማት እና ለቀጣናዊ ትብብር ቅድሚያ እንደምትሰጥ ጠቁመው፤ ለአብነትም በውጭ እና የኢኮኖሚ ፖሊሲዋም በግልጽ መቀመጡን ተናግረዋል።
የኢኮኖሚና ሌሎች የሪፎርም ተግባሯቷም የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን ጨምሮ ከምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ እና ሌሎች ዋና ዋና አኅጉራዊ ማዕቀፎች ጋር እንዲሰናሰል ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት አመላክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ቀጣናዊ ትብብር በአፍሪካ ውስጥ የግል ኢንቨስትመንት በስፋት ለማንቀሳቀስ እንደሚረዳም አስረድተዋል።
ለዚህም ፖሊሲዎችን በማጣጣም፣ ገበያዎቻችንን በማገናኘትና ድንበር ተሻጋሪ መሠረተ-ልማቶችን በማስፋት በይበልጥ መከናወን እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ያላትን ዝግጁነት ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
በአኅጉሪቱ መንግሥታት፣ በልማት የፋይናንስ ተቋማትና በግሉ ዘርፍ አጋሮች መካከል ቀጣናዊ ፕሮጀክቶችን ማሳለጥ፤ የንግድ መሰናክሎችን በማስወገድ፣ አፍሪካን የተዋሃደ እና ተወዳዳሪ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ያስችላል ሲሉ ማብራራታቸዉን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡