የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በትግራይ ክልል ይከበራል

You are currently viewing የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በትግራይ ክልል ይከበራል

AMN ህዳር 19/2018

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ህዳር 24 ቀን 2018 ዓ.ም በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ እንደሚከበር የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

ቀኑ “አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማኅበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማኅበራዊ እድገት” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበርም ተገልጿል።

አካል ጉዳተኞች በፍትሕ፣ ጤና፣ የስራ ዕድል እና በመሳሰሉት ተደራሽ እንዲሆኑላቸው መንግስት እየሰራ መሆኑን የገለጹት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሁሪያ አሊ፤ በዓሉ ሲከበር የ አካል ጉዳተኞች በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የእኩል ዕድል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ ለማቅረብ የሚያስችል ቅስቀሳ ማድረግ የሚቻልበት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም፤ በዘርፉ ቀጥተኛ ሚና ያላቸውን አካላት ለማስገንዘብና አስፈላጊውን ኃላፊነት እንዲወጡ ለማስቻል የሚያግዙ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን መስራት ከበዓሉ መከበር ጋር ተያይዘው ከተቀመጡ ዓላማዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌደሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች መቻላቸውን የሚያረጋግጡ በርካታ ተግባራት የበዓሉ አከባበር አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓሉ በሚከበርባት ትግራይ ክልል ለሚገኙ አካል ጉዳተኞችም የተለያዩ ድጋፎች እንደሚደረግ ተገልጿል።

በላይሁን ፍስሃ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review