ልጆቻቸውን ያሰለጠኑና ያሰለፉ አሰልጣኞች

You are currently viewing ልጆቻቸውን ያሰለጠኑና ያሰለፉ አሰልጣኞች

AMN – ህዳር 19/2018 ዓ/ም

በአውሮፓ ተወዳጅ ሊጎች ውስጥ አይረሴ ክስተቶች ተከስተዋል፡፡ ከነዚህ መካከል አባት አሰልጣኝ ልጅ ተጨዋች ሆነው የተመለከትንባቸውን አጋጣሚዎች ይታወሳሉ፡፡

ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ለቁጥር የሚያዳግቱ ስኬቶችን ያስመዘገቡት ስኮትላንዳዊ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ልጃቸውን ዳረን ፈርጉሰንን ወደ ማንችስተር ዩናይትድ አካዳሚ ያስገቡ አሰልጣኝ ናቸው፡፡

ዳረን የአካዳሚ ስልጠናውን አጠናቆ ለዋናው ቡድን 28 ጨዋታዎችን ካደረገ በኋላ ለዎልቭስ፣ ስፓርታ ሮተርዳምና ፒተርቦሮው ዩናይትድ ተጫውቶ በ2008 ነበር ጫማውን የሰቀለው፡፡

እንግሊዛዊ ሃሪ ሬድናፕ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ተመልካቾች የማይረሷቸው አሰልጣኝ ናቸው፡፡

የቶትንሃምና ፖርትስማውዝ የቀድሞ አሰልጣኝ ሬድናፕ የአሰልጣኝነት ስራን ሲጀምሩ ልጃቸውን ዢሚ ሬድናፕን ለበርንማውዝ አካዳሚ አስገቡት፡፡ ከዚያም ለበርንማውዝ ዋናው ቡድን 18 ያህል ጨዋታዎችን ካሳለፉት በኋላ ከክለቡ ጋር ተያይዘው ተባረሩ፡፡

የሪያል ማድሪድ ታሪካዊ ተጨዋችና አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ሁለቱንም ልጆቹን ያሳደገው ማድሪድ ውስጥ ነው፡፡ ፈረንሳዊ አለቃ ኢንዞን እና ሌላኛውን ልጁን ሉካን ለማድሪድ ዋናው ቡድን አሰልፎ ይህንኑ ታሪክ ተጋርቷል፡፡

የአትሌቲኮ ማድሪድ የወቅቱ አሰልጣኝ ዲየጎ ሲሞኒ ልጃቸው ጉሊያኖ ሲሞኒን በማሰለፍ ሌላኛው ባለ ታሪክ ናቸው፡ አርጀንቲናዊ አሰልጣኝ 67 ጨዋታዎች ላይ ልጃቸውን አሰልፈዋል፡፡

የማንችስተር ዩናይትድ የቀድሞ ተከላካይ ዳሊ ብሊንድ አባት ዳኒ ብሊንድ የተዋጣላቸው አሰልጣኝና ተጨዋች ነበሩ፡፡ በሐገራቸው ክለቦች ስፓርታ ሮተርዳምና አያክስ ተጫውተው ያሳለፉት ዳኒ ብሊንድ በአሰልጣኝነት ዘመናቸው ኔዘርላንድስን ሲመሩ ልጃቸው ዳሊ ብሊንድን 14 ጊዜ የመሰለፍ እድል ሰጥተውታል፡፡

ለኤሲ ሚላን መጫወትን የቤተሰብ ያደረጉት የማልዲኒ ቤተሰቦችን ታሪክ ብዙዎች አይረሱትም፡፡ የቀድሞ ተጨዋች፤ በኋላ አሰልጣኝ ሆነው ክለቡን የመሩት ሴዛር ማልዲኒ የመጀመሪያው ባለ ታሪክ ናቸው፡፡ ልጃቸውን ፓውሎ ማልዲኒን 23 ጊዜ ለሚላን ከተማው ክለብ በማሰለፍ የታሪኩ ተጋሪ ናቸው፡፡ የልጅ ልጃቸው ዳንኤል ማልዲኒም ለኤሲ ሚላን ተጫውቶ አሳልፏል፡፡

ትናንት ምሽት በዩሮፓ ሊግ የአምስተኛ ዙር ጨዋታ ፌይኖርድ በሜዳውና ደጋፊው ፊት በሴልቲክ 3ለ1 ሲሸነፍ የክለቡ አሰልጣኝ ሮቢን ቫንፔርሲ ሌላ ታሪክ ጽፏል፡፡ የአርሰናልና ማንችስተር ዩናይትድ የቀድሞ አጥቂ ቫንፔርሲ የ19 ዓመት የበኩር ልጁን ሻክዊል ቫንፔርሲን ቀይሮ አስገብቶ አጫውቷል፡፡

በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ውስጥ አባት አሰልጣኝ እንዲሁም ልጅ ተጨዋች ሆነው የሰሩት እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ለዛሬ ዋና ዋና ያልናቸውን አስታወስናችሁ፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review