ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሐሳብ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና መስጠታቸው ይታወቃል። በዚህ መድረክ ላይ ቱሪዝምን ከቅርስነት ወደ ቁርስነት መቀየር እንደሚገባ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ቅርስ አለ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ነገር ግን ቁርስ መሆን እንዳልቻለ ተናግረዋል።
ትላልቅ ቅርስ ይዘን ወደ ቁርስ መቀየር ባለመቻላችን የገንዘብ ምንጭ መሆን የሚችሉ ቅርሶች መጠገን እንኳን ወደማንችልበት ደረጃ ወርደናል ብለዋል።
አሁን ያለው ጎብኚ ቅርሱ ብቻ ስላለ መጥቶ የሚያይ አለመሆኑን በማንሳት፣ ለሚያወጣው ወጪ የሚመጣጠን አገልግሎት፣ ከባቢ እና ሰላም መኖሩን ማረጋገጥ እንደሚፈልግም አስገንዝበዋል።
እንደ ሀገር መስህቦች አሉን ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ነገር ግን በቂ ማረፊያዎች አለመኖራቸው ችግር መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም። መፍትሔውም መስሕቦችን እና ማረፊያዎችን አዋሕዶ መሥራት መሆኑን ነው የገለጹት፤ ማረፊያው በሌለበት መስህብ ስላለ ብቻ በበቂ ደረጃ ሰው አይመጣም ሲሉም ነው ያስረዱት።
ባለፉት ሦስት ወራት ወንጪን የጎበኙት አሥር ሺህ የሳዑዲ ጎብኚዎች መስህቡ ብቻውን ባለበት ሰዓት ሳይመጡ አሁን ማረፊያ ሲሠራ መምጣታቸው ቅርስን ወደቁርስነት መቀየር ለመቻሉ ማሳያ አድርገው አቅርበዋል።
በታምራት ቢሻው