በሚቀጥሉት አስር ቀናት ወደ ሀገሪቱ የሚነፍሰው ደረቅ እና ቀዝቃዛ አየር ተጠናክሮ ይቀጥላል

You are currently viewing በሚቀጥሉት አስር ቀናት ወደ ሀገሪቱ የሚነፍሰው ደረቅ እና ቀዝቃዛ አየር ተጠናክሮ ይቀጥላል

AMN ህዳር 22/2018 ዓ.ም

በሚቀጥሉት አስር ቀናት ከሳይቤሪያ ከፍተኛ የአየር ግፊት ላይ በመነሳት ወደ ሀገሪቱ የሚነፍሰው ደረቅ እና ቀዝቃዛ አየር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኤኤምኤን በላከው መግለጫ እንደገለፀው በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት አካባቢዎች ላይ ቀጣይነት ይኖረዋል።

ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በጥቂት የደቡብ እና የደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናቶች ላይ በተዳከመ ሁኔታ ቀጣይነት ይኖራቸዋል።

በዚህም የደቡብ ኦሮሚያ ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡባዊ ዞኖች እና የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ዞኖች በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ በጣም አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ገልጿል።

በሌላ በኩል ከሚኖረው የደመና ሽፋን ላይ በመነሳት በጥቂት የሰሜን፣ መካከለኛውና ደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ ባህርዳር ዙሪያ፣ አዊ ፣ በምዕራብና ምስራቅ ጎጃም አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናት ወቅቱን ያልጠበቀ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም ትንበያው አብራርቷል።

የምዕራብ ኦሮሚያ ክልል ዞኖች፣ አርሲ እና ምዕራብ አርሲ፤ ባሌ እና ምስራቅ ባሌ ዞኖች፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ እና የማኦኮሞ ልዩ ዞን፤ የጋምቤላ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖችም አልፎ አልፎ ወቅቱን ያልጠበቀ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ።

ስለሆነም በሚኖሩት ደረቅ ቀናቶች የደረሱ ሰብሎች መሰብሰብ አስፈላጊ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል።

በሌላ በኩል ከሳይቤሪያ ከፍተኛ የአየር ግፊት ላይ በመነሳት ወደ ሀገሪቱ የሚነፍሰው ደረቅ እና ቀዝቃዛ አየር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩም በመግለጫው ተብራርቷል።

በዚህም የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በተለይም በሰሜን፣ ምስራቅ፣ መካከለኛውና ደቡብ ደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የለሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ ከአምስት ዲግሪ ሴልሺየስ በታች እንደሚሆን ትንበያው ያሳያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review