አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመዘርጋት የተጀመረውን ለውጥ ማጠናከር ይገባል

You are currently viewing አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመዘርጋት የተጀመረውን ለውጥ ማጠናከር ይገባል

AMN – ህዳር 22/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የተተከሉ ከሳተላይት ያለማቋረጥ መረጃን የሚቀበሉ 10 ጣቢያዎችን ስራ አስጀምሯል ፡፡

ጣቢያዎቹ በቋሚነት መሬት ላይ የሚተከሉና የሳተላይት መረጃዎችን ያለማቋረጥ የሚቀበሉና የሚተነትኑ መሆናቸው ታውቋል።

ዛሬ ሥራ የጀመሩት ጣቢያዎች ከተሞች ከዚህ ቀደም የሚታወቁበትን ውስብስብና ኋላ ቀር አሰራርን የሚቀይሩ መሆናቸውን የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን ተናግረዋል።

በተለይም የከተሞችን መሬት ዘመናዊ በሆነ አሰራር ማስተዳደር እንዲቻልና የካርታና የካዳስተር ስራን ጊዜንና ወጪን በቆጠበ መልኩ ለመምራት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በቀጣይ 14 ከሳተላይት ያለማቋረጥ መረጃ የሚቀበሉ ጣቢያዎች /CORS/ ለመገንባት እየሰራ እንደሚገኝ ሚንስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉቀን ቀሬ በበኩላቸው እንደሀገር የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ የማሳለጥ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀው አሰራሮችን ከአናሎግ ወደ ዲጂታል የመቀየሩ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በቀጣይም ሚኒስቴሩ ከሳተላይት መረጃ የሚቀበሉ ጣቢያዎችን ለማስፋፋት ተናቦና ተቀናጅቶ እንደሚሠራ አብራርተዋል ።

የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ አሁን ላይ ስራ የጀመሩት መረጃ ተቀባይ ጣቢያዎች አስተማማኝ እና ትክክለኛ መረጃዎችን መስጠት የሚችሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ቴክኖሎጂው በኮንስትራክሽ፣ በትራንስፖርት፣በግብርና እንዲሁም በማዕድን ዘርፍ ወቅታዊና አሁናዊ መረጃን መስጠት የሚችሉ ናቸው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ወደ ስራ የገቡ 10 የመረጃ ጣቢያዎች እንዳሉ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ዛሬ ወደ ስራ የገቡትን ጨምሮ በሁለት አመታት ውስጥ ቁጥሩን 34 በማድረስ የክልል ዋና ከተሞች የመረጃ ተደራሽነት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል ።

ይሕ የሳተላይት መረጃን ያለማቋረጥ የሚቀበል ጣቢያ Continuous Operating Reference Station /CORS/ የአንድን ቦታ መገኛ ከጂ ፒ ኤስ ሳተላይቶች 24 ሰዓት በመቀበል ከፍተኛ ጥራት ያለው መረጃ የሚያቀርብና የሚያደራጅ እንደሆነም ተገልጿል።

በታምሩ ዴምሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review