የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከጉሙሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ባከናወነው ኦፕሬሽን ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በድሬዳዋና በሶማሌ ክልል መያዙን ገልጿል።
የፀረ-ኮንትሮባንድ ፖሊስ መምሪያ የሬጅመንት 14 አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር አበበ ጎባ እንደገለፁት ኮድ 3 ኢት 24984፣ ኮድ 3 ኢት A39800፣ ኮድ 3 ድሬ 07700፣ ኮድ 3 ኢት 2709 የሆኑ ተሽከርካሪዎች መነሻቸውን ከሶማሌላንድ መድረሻቸውን ደግሞ ድሬዳዋ በማድረግ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ጭነው በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን አይሻ ወረዳ አካባቢ ቢያቆቤና በደምበል ወረዳ አርሙከሌ ቦታ እንዲሁም በድሬደዋ መግቢያ ፈንጅስታ በሚባል ቦታ ላይ ተይዘዋል።
ተሽከርካሪዎቹ ከጉሙሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በተካሄደ ኦፕሬሽን ተይዘው በተደረገው ፍተሻ ቆርቆሮ፣ ፌሮ ብረት፣ የተሽከርካሪ ጎማ እና የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን መያዛቸውን የገለፁት ዋና ኢንስፔክተር አበበ የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹም ለድሬዳዋ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ገቢ መደረጋቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡
ሕብረተሰቡ ኮንትሮባንድ በሀገር ኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ በተለይ በኅብረተሰብ ጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በመረዳት በኮንትሮባንድ መከላከል እና መቆጣጠር ላይ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ የበለጠ በማጠናከር መቀጠል እንዳለበት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡