በየቦታው የሚጣሉ እና የሚቃጠሉ ወረቀቶችን ለእኛ ስጡን

You are currently viewing በየቦታው የሚጣሉ እና የሚቃጠሉ ወረቀቶችን ለእኛ ስጡን

AMN- ህዳር 23/2018 ዓ.ም

ባለንበት ወቅት ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ወድቃለች፣ ለዚህ ዋነኛ መንስዔ የሆነው ደግሞ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓታችን አለመዘመን ነው፡፡

የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸውን ወረቀቶች ከመጣልና ከማቃጠል ይልቅ ወደ ምርት በመቀየር እየሰራ የሚገኘው ወጣት ዘይኑ ኢብራሂም ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸውን ወረቀቶች ወደ ሀብት ወደ ገንዘብ መለወጥ ይቻላል የሚለው ባለሙያው፣ ያገለገሉ ወረቀቶች እና ካርቶኖች በተለያየ ሂደት አልፈው ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ምርቶች እንደሚዘጋጅባቸውም አንስቷል፡፡

በተለያዩ ሂደቶች ውስጥ ያለፉት ያገለገሉ ወረቀቶች፣ ለማተሚያ ቤቶች ግብዓት ፣ ለመዝገብ መስሪያ፣ ለሰነድ ማህደር (ቦክስ ፋይሎች) መስሪያነት እና ለጫማ ማጠንከሪያ የሚሆኑ ጠንካራ ወረቀቶች እንደሚሰራባቸው ነው የተናገረው ፡፡

ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ሂደት የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸውን ወረቀቶች መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚረዳው ማሽን፣ የወረቀት ዘንቢል መስሪያ የሚሆነውንም ግብዓት እንደሚያመርት ተናግሯል፡፡

ከዚህ ቀደም ቢን ካርዶችን ከነጋዴዎች በውድ እየገዙ ማህደር (ቦክስ ፋይሎችን) በሙቅ እየለጠፈ ይሰራ እንደነበር ወጣት ዘይኑ ያወሳል፡፡

የማያስፈልጉትን ወረቀቶች ሲጣሉ እና ሲቃጠሉ ከሚደርሰው የገንዘብ ኪሳራ ባለፈ፣ አካባቢን በማቆሸሽ እና በመበከል ችግር እንደሚያስከትልም ይናገራል፡፡

በመሆኑም ወረቀቶች ከማስወገድ ይልቅ ለምን መልሰን አንጠቀምበትም በሚል ሃሳብ ወደዚህ ሥራ እንደገባ አጫውቶናል፡፡

አሁን ላይ ያመረታቸውን ምርቶች ለማተሚያ ቤቶች፣ መጽሐፍ ለሚጠርዙ ሰዎች፣ የዩኒቨርሲቲ መመረቂያ ፎልደሮች ለሚሰሩ፣ መዝገብ ለሚያመርቱ ማተሚያ ቤቶች እና ለጫማ ፋብሪካዎች እየቀረበ እንደሚገኝ ነው የነገረን ፡፡

አሁንም ወረቀቶችን የሚጥሉ እና በየቦታው እያቃጠሉ የሚያስወግዱ ሰዎች እንዳሉ በማንሳትም፣ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ለኛ ቢሰጡን እኛ ወደ ምርት እንቀይራቸዋለን ብሏል ፡፡

አሁን ላይ እያመረተ ያለው ምርት ከውጭ የሚገባውን ተመሳሳይ ምርት ከማስቀረት ባለፈ፣ በዋጋ ደረጃም በግማሽ የሚቀንስ መሆኑን ነው ወጣት ዘይኑ ኢብራሂም ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበረው ቆይታ የነገረን ፡፡

በታምራት ቢሻው

#አዲስሚዲያኔትዎርክ

#Ethiopia

#addisababa

#ሥራፈጣሪ

#አዲስአበባ

#ኢትዮጵያ2018

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review