በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራዎች የመዲናዋ ነዋሪዎችና ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የመጡ እንግዶችን ብቻ ሳይሆን ከዉጭ ሃገራት የመጡ ዜጎችን ጭምር በማስደመም ላይ ይገኛሉ፡፡
አዲስ አበባ አሁን ላይ ብዙዎች ሊጎበኟትና ሊያዩዋት የሚናፍቋት የአፍሪካ መዲና ሆናለች፡፡

ሜክሲኮ አከባቢ የእግር ጉዞ ሲያደርጉ እና ፒያኖ ሲጫወቱ ከነበሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ሄኖክ ድንቁ ለኤኤምኤን ዲጂታል ሚዲያ እንደተናገረዉ የአዲስ አበባ አሁናዊ ለውጥ ከአውሮፓ ሀገራት ጋር እንደሚነጻጸር ነዉ፡፡
አዲስ አበባ ከውበቷ ባሻገር ሰላም እና ጸጥታዋ እጅግ በጣም የሚያስደስት ነዉ፤ ይህንን ልማትና አስተማማኝ ሰላም ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማስቀጠል ደግሞ የነዋሪዉ ሃላፊነት ነዉ ሲል ተናግሯል፡፡
ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ ዘላለም ታደሰ በበኩሉ ከተማዋ የተለያዩ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በወንድማማችነት የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን በመጠቆም ይህም ሌላኛው የአዲስ አበባ ዉበት መሆኑን ይገልጻል፡፡

ከጀሞ አከባቢ ለሽርሽር ወደ ሜክሲኮ መምጣቷን የምትናገረዉ ሀያት መሀመድ በበኩሏ በከተማዋ የለሙ የኮሪደርና የወንዝ ዳር ልማት ስራዎች ወጣቶችን አልባሌ ቦታ እና ከሱስ መታደጋቸዉን ገልጻለች፡፡
ከአርሲ አካባቢ መምጣቱን የሚናገረዉ ወጣት ታደሰ ዘነበ በመዲናዋ ከአሁን ቀደም የነበረዉ የሚሰነፍጥ ሽታ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማቱ በዉብ አበቦች፤ በመልካም መዐዛ ፤ በመዝናኛ ስፍራዎች እና አይንን በሚማርኩ ልማቶች ተተክቶ በማየቱ መደነቁን ይናገራል፡፡
የፎቶ ግራፍ ባለሞያዉ ጸጋዬ ኢያሱ በበኩሉ የአዲስ አበባ ልማት ለሃገር ዉስጥና ለዉጭ ሃገራት ዜጎች ተዝናቶትን ለእኛ ደግሞ የስራ እድል ፈጥሮልናል ሲል ለኤኤምኤን ተናግሯል፡፡
አዲስ አበባ በየቀኑ አዲስ እየሆነች ከመምጣቷም በላይ ለማህበራዊ ሚዲያ የሚሆን ቪዲዮ ለመስራት ምቹ መዲና ሆናልናለች የምትለዉ ደግሞ ወጣት አዲስአለም መኮንን ናት።
በስፈራው ያገኘናቸው ወጣቶች ሁሉም በአንድ ቃል የሚገልፁት አዲስ አበባ እንደ ስሟ በየቀኑ አዲስ እየሆነች መምጣቷን ነዉ፡፡
በፍሬሕይወት ብርሃኑ