ግላኮማ ወይም የዓይን ግፊት ከዓይን ወደ ጭንቅላት መልዕክት የሚወስደው ኦኘቲክ (Optic) የተሰኘ ነርቭ ጉዳት ሲደርስበት የሚከሰት የዓይን በሽታ ነው፡፡
በዓለም ላይ ወደ 80 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በግላኮማ ወይም በዓይን ግፊት ምክንያት የዓይን ብርሃናቸውን እንደሚያጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በዓይን ውስጥ የሚገኝ ውሃ መሰል ፈሳሽ ዓይን ዳር ዳር ባሉ ቀዳዳዎች አማካኝነት እየወጣ የደም መቀላቀል የሚኖርበት ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ቀዳዳዎቹ ከጠበቡ ፈሳሹ ለመውጣት በሚፈጠር ግፊት የዓይን ነርቮችን ያጠቃል፤ ይህም ግላኮማን ወይም የዓይን ግፊት በሽታን ያስከትላል፡፡

ግላኮማ ወይም የዓይን ግፊት በሽታ ሁለት ዓይነት ሲሆን ኦኘን አንግል እና ክሎዝድ አንግል በመባል ይታወቃል፡፡
ኦኘን አንግል ግላኮማ በመባል የሚታወቀው ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኞቹ ከሰሀራ በታች በሚገኙ ሀገራት ይከሰታል፤ ክሎዝድ አንግል የተሰኘው ግላኮማ በአብዛኛው ሴቶችን የሚያጠቃ ነው፡፡
የአይን መስታወት ንቅለ ተከላ ሰብ ስፔሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ኤሊያስ ኃይሉ ዓይነስውርነትን ከሚያስከትሉ የዓይን ችግሮች አንዱ የሆነው ግላኮማን መመለስ የማይቻል የዓይን ጉዳት መሆኑ በሌላ ምክንያት ከሚከሰት ዓይነ ስውርነት የተለየ ያደርገዋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ከ8ዐ በመቶ በላይ ህመሙ ምንም አይነት ምልክት አያሳይም፤ ለዚህም ተጠቂዎች የነርቭ ጉዳቱ ከደረሰና እይታ ከቀነሰ በኃላ ወደ ህክምና በመምጣታቸው አክሞ ለማዳን አዳጋች ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

2ዐ በመቶ የሚሆኑ የበሽታው ተጠቂዎች ከግራ ወይም ከቀኝ ያለን ምስል የመለየት አቅም መቀነስ፣ የዓይን ውጋት፣ መቅላት፣ ቁስለት፣ ብርሃን መፍራት፣ ብዥታ፣ ዕንባ፣ አልፎ አልፎ የዓይን ቆብ መርገብገብ፣ አንዳንዴ ብሌን ወይም ሙሉው የዓይን መጠን መጨመር የግላኮማ ወይም የዓይን ግፊት በሽታ ምልክቶች ናቸው፡፡
ምልክቶቹ ከታወቁ የዓይን ግፊቱን ዝቅ በማድረግ እንደ የዓይን ነርቭ ጉዳት መጠን፤ ግፊቱን የሚቀንሱ የዓይን ጠብታና በቀዶ ሕክምና የተጠራቀመውን ውሃ መሰል ፈሳሽ በሌላ መንገድ እንዲወጣ በማድረግ ጉዳቱን ባለበት ማቆም ይቻላል ሲሉ የአይን መስታወት ንቅለ ተከላ ሰብ ስፔሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ኤሊያስ ኃይሉ ለኤኤምኤን ተናግረዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው