የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሱፐር ካፕ ውድድርን ለሳውዲ አረቢያ አቻው ከሸጠ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት እስከ 2029 በሚዘልቀው ውላቸው፤ የሱፐር ካፕ ውድድር በአራት ክለቦች መካከል በየዓመቱ ሳውዲ ላይ ይደረጋል፡፡
በዚህ መሰረት የዚህ ዓመቱ የስፔን ሱፐር ካፕ በመጪው ጥር ወር በሳውዲ ጂዳ ላይ በባርሴሎና፣ ሪያል ማድሪድ ፣ አትሌቲኮ ማድሪድና አትሌቲክ ቢልባኦ መካከል ይደረጋል፡፡ በዚህ የተነሳም በላሊጋው መርሃ ግብሮች ላይ ቀደም ብሎ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡
በ19ኛ ሳምንት የስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ከአትሌቲኮ ማድሪድና ሪያል ማድሪድ ከአትሌቲክ ቢልባኦ ጋር ያደርጓቸው የነበሩ ጨዋታዎች ዛሬና ነገ ይከናወናሉ፡፡ ዛሬ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ሲል በካምፕ ኑ ባርሴሎና ከአትሌቲኮ ማድሪድ ይጫወታል፡፡
በላሊጋው 14ኛ ሳምንት ባርሴሎና አላቬስን 3ለ1 እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪድ ኦቪዶን 2ለ0 አሸንፈው የሚገናኙበት ጨዋታ ይሆናል፡፡
የካታሎኑ ክለብ በሪያል ማድሪድ 2ለ1 ከተሸነፈ ወዲህ ያደረጋቸውን አራቱንም የላሊጋ ጨዋታዎች አሸንፏል፡፡
አትሌቲኮ ማድሪድ በበኩሉ ሪያል ማድሪድን 5ለ2 ያሸነፈበትን ጨምሮ ባለፉት 13 የላሊጋ ጨዋታዎቹ አልተሸነፈም፡፡
ባለፈው ሳምንት የዲየጎ ሲሞኒ ስብስብ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢንተር ሚላንን 2ለ1 ማሸነፉ፤ ባርሴሎና በተቃራኒው በቼልሲ 3ለ0 መሸነፉ አይዘነጋም፡፡
ባርሴሎና በ34 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ በ31 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የሚያከናውኑት ተጠባቂ ጨዋታ ነው፡፡
ነገ ሌላኛው ጨዋታ በአትሌቲክ ቢልባኦና ሪያል ማድሪድ መካከል ይደረጋል፡፡
በታምራት አበራ