የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የሀገሪቱን የፋይናንስ ስርዓት በማሳለጥ የጎላ ሚና እንዳለው የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።
ሁለተኛው ቀጣናዊ የካፒታል ገበያ ጉባኤ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን መፃኢ የፋይናንስ ስርዓት የሚያሳልጥ መሰረታዊ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ አካታች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል።
ማሻሻያው ወደ ተሟላ ትግበራ ከገባ ወዲህ ማክሮ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት ሁሉን አቀፍ ዕድገት ማረጋገጥ በሚያስችል ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሀገር ውስጥ ገቢን በማስፋት ዕምርታዊ ለውጥ መመዝገቡንም ገልጸዋል።
በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ ሪፎርም መደረጉን ገልጸው፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያሳድግ ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
በኢኮኖሚ ሪፎርሙ መሰረት ወደ ሥራ የገባው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ስርዓት በማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ያሉት ሚኒስትሩ፥ ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር ለኢኮኖሚያዊ ሽግግር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ተዓማኒ፣ እውነተኛና ተስማሚ የፋይናንስ ምህዳር ለመፍጠር በተቋማት መካከል ጠንካራ ትብብር መፍጠር ይገባል ብለዋል።
በአግባቡ የተደራጀ እና የተሟላ መሰረተ ልማር ያለው የካፒታል ገበያ ስርዓት የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለማሳደግና ከዓለም የፋይናንስ ተቋማት ጋር ለማስተሳሰር ያግዛል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ይኸውም የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለኢንቨስተሮች መተማመኛ እንደሚሆን ገልጸዋል።