“ከ158 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶችና ሴቶች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል” – የሥራና ከተማ ልማት ቢሮ

You are currently viewing “ከ158 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶችና ሴቶች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል” – የሥራና ከተማ ልማት ቢሮ

AMN – ሕዳር 24/2018

ባለፉት አራት ወራት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁትን ጨምሮ ከ158 ሺህ 138 ለሚበልጡ ወጣቶች እና ሴቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክሕሎት ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየደረጃው ሲካሄዱ የቆዩት የሥራ አውደ ርዕዮች መጠናቀቅን ተከትሎ፣ በመዲናዋ ለሚገኙ ከ30 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች “የአንድ ጀምበር የስራ ዕድል” ፈጠራ ንቅናቄ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም አካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ እና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክሕሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ “የአንድ ጀምበር የሥራ ዕድል” በተለያዩ ጊዜያት የሥራ ዕድል ይፈጠርልን ጥያቄ ለነበራቸው እና ተደራጅተው ወደ ሥራ ሳይገቡ ለቆዩ ሥራ ፈላጊዎች የተሰጠ መልስ መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው እና የሥራ ዕድል ከሚፈጥሩ መንግሥታዊ ተቋማት ጋር በመሆን ከ30 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ትስስር እና የመስሪያ ቦታ እንዲያገኙ በማድረግ ዘላቂ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

ቢሮው በየዓመቱ ከ300 ሺህ ለሚበልጡ ሥራ ፈላጊዎች እንደ ፍላጎታቸው የቴክኒካል ክህሎት ሥልጠና በመስጠት በቅጥር እና በማደራጀት የሥራ ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በመዲናዋ በ2018 በጀት ዓመት ከ350 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት የቢሮው ኃላፊ ባለፉት አራት ወራት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁትን ጨምሮ ከ158 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች እና ሴቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

በወንድማገኝ አሰፋ

#30ሺህየሥራዕድል

#የአንድጀምበርየሥራዕድል

#ሥራናክህሎትቢሮ

#ከተረጂነትወደአምራችነት

#Jobcreation

#AddisAbaba

#AMN

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review