የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን መከበር ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የጎላ አስተዋጽኦ አበርክቷል

You are currently viewing የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን መከበር ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የጎላ አስተዋጽኦ አበርክቷል

AMN ህዳር 24/2018

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን መከበር ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።

በአማራ ክልል ደረጃ 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ማጠቃለያ መርሀ ግብር በደብረብርሃን ከተማ በድምቀት ተከብሯል። በበዓሉ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንዳሉት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ ለመኖር የተስማሙበት ነው።

ቀኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን በአደባባይ ወጥተው የሚገልጡበት እንደሆነም ተናግረዋል።

በመሆኑም ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል የፌደራል ስርዓት እንዲኖር በማድረግ ህብረ ብሔራዊነትን በማጠናከር ህዝቦች በአንድነት ተሳስረው እንዲኖሩ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አመልክተዋል። የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ለዲሞክራሲ ግንባታ መሰረት የጣለ ነው ሲሉም አክለዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ፈጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋየ፤ በዓሉ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በአስተምህሮት፣ በበጎፈቃድ አገልግሎት፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጎልበት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መንገድ ሲከበር መቆየቱን ተናግረዋል ።

የቀኑ አከባበር ህግ እና ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ህዝቦች ባህል፣ ወጋቸውንና እሴቶቻቸውን ተጠቅመው የውል ትርክት ለመገንባት እድል የፈጠረ ነው ብለዋል።

የዘንድሮ አከባበር የታላቁ ህዳሴ ግድብ የተጠናቀቀበትና የይቻላል መንፈስን የገነባንበት እና ሌሎች ለሀገር የሚጠቅሙ ሜጋ ፕሮጀክቶችን አቅደን ስራ የገባንበት ወቅት ላይ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ከጀመረ ወዲህ የህዝቦች አብሮነት፣ የአንድነትና የመደጋገፍ አሴት እያደገ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ናቸው።

በከተማው የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት መስፋፋትና ማደግ የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ በመምጣቱ ከህገ መንግስቱ ቱሩፋት የተገኘ መሆኑን አስታውቀዋል። ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ መሰረት ቀጸላ የቀኑ መከበር ህገመንግስታዊ አስተምህሮትን ይበልጥ ለማጎልበት ያግዛል ብለዋል።

በተለይ ሴቶች በህገመንግስቱ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው እለቱ ለሴቶች ልዩ እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ ብስራት ታደለ በበኩላቸው የቀኑ መከበር ዜጎች እርስ በእርሳቸው በመተዋወቅ የነገን ተስፋ በጋራ ለመሰነቅ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

በተለይም ባህልን ጨምሮ ማህበረሰባዊ እሴቶችን ለመጠበቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ የጎላ ሚና እንዳለው መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ በዓሉ እንደሀገር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳእና ከተማ የፊታችን ህዳር 29 ቀን 2018 ዓም እንደሚከበር ታውቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review