የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የ500 ሺህ ዩሮ ዋጋ ግምት ያላቸው ዘመናዊ የፎረንሲክ ላብራቶሪ መሳሪያዎችን ከአውሮፓ ህብረት በድጋፍ አግኝቷል።
ዘመናዊ የፎረንሲክ ላብራቶሪ መሳሪያዎቹን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ያስረከቡት በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤመስበርገር ናቸው።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ድጋፉ ኢትዮጵያ የፍትህ እና የህግ አስከባሪ ተቋማትን የበለጠ ውጤታማ እና ቀልጣፋ ለማድረግ በትጋት እየሰራችበት ባለችበት ወቅት መሆኑን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በድጋፍ የተገኙት ዘመናዊ የፎረንሲክ መሣሪያዎች ሳይንሳዊ ምርመራዎች፣ የወንጀል ስፍራ ትንተና፣ የጣት አሻራ መለያ፣ የጦር መሳሪያ መረጃ ትንተና እና የክትትል ማስረጃዎችን መመርመር የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የተደረገው ድጋፍ የፍትህ ሥርዓቱን የሚያሳድጉና መንግሥት እያደረገ ያለውን የፀጥታ ዘርፍ ማሻሻያ ኢኒሼቲቭ (Security Sector Reform Initiative) ለማሳካት የላቀ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት ላደረገው ዘመናዊ የፎረንሲክ ላብራቶሪ መሳሪያዎች ድጋፍ በኢትዮጵያ መንግስት እና በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤመስበርገር በበኩላቸው ዘመናዊ የፎረንሲክ መሳሪዎቹ በአውሮፓ ህብረት የወንጀል ፍትህ ድጋፍ ማሻሻያ ፕሮግራም ማዕቀፍ ውስጥ የቀረቡ ልዩ የፎረንሲክ መሳሪያዎች መሆናቸዉን ገልጸዋል።
የፎረንሲክ ምርመራ አቅምን በመደገፍ፣ የአውሮፓ ህብረት በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖሊስን ውጤታማነት፣ ተአማኒነት እና ግልፀኝነት ላይ ኢንቨስት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ድጋፉ የህግ አስከባሪ ተቋማትን ለማጠናከር እና የህዝብ አመኔታን ለመገንባት በማሰብ በወንጀል ፍትህ ሰንሰለት ውስጥ የተደረጉ ማሻሻያዎችን ለመደገፍ ከሚደረገው ሰፊ የአውሮፓ ህብረት ጥረት አንዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንድትቀጥል የአውሮፓ ህብረት አስተማማኝ አጋር ሆኖ እንደሚቀጥል መግለጻቸዉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል።