የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ “በግብፅ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የሚሰጡ መግለጫዎችና የተደበቁ ማስፈራሪያዎች የካይሮ መንግሥት የ21ኛው ክፍለ ዘመን እውነታዎችን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን የሚያሳዩ ናቸው” ብሏል።
“በቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ ውስጥ የተዘፈቁ” ጥቂት የግብጽ ባለሥልጣናት በዓባይ ወንዝ ውሀ ላይ አሁንም ብቸኛ ባለመብት እንደሆኑ እያሰቡ ነው ያለው መግለጫው እነዚሁ ባለስልጠናት የአፍሪካ ቀንድን በተለይም ኢትዮጵያን የማፈራረስ አጀንዳ እያራመዱ ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ እንደሀገር አፍሪካዊነትን የማቀንቀን እና ጸረ ቅኝ ግዛት ትግሎችን በአሕጉሪቱ ውስጥ የማቀጣጠል የረዥም ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር በመሆኗ ግብጽ ለማስወገድ የተቸገረችውን “የቅኝ ግዛት ቅሪቶች” የምታስተናግድበት ምንም አይነት ቦታ የላትም ነው ያለው መግለጫው።
ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ ልክ እንደሌሎች የናይል ተፋሰስ ሀገሮች ሁሉ የዓባይን ወንዝ የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም ሙሉ መብት አላት። ለናይል ተፋሰስ ውሀ 86 በመቶ ድርሻ ይዞ ገባር የሆነውና ከሀገሪቱ 70 በመቶውን ያህል መሬት የሚያካልለውን ዓባይ ፍትሐዊ፣ ምክንያታዊ እና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ኢትዮጵያ የማንንም ፈቃድ የመጠየቅ ግዴታ እንደሌለባት በአጽንዖት ገልጿል።
የኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዕውን መሆን ያረጋገጠው አፍሪካ ራሷን እየቻለች እና በለውጥ መንገድ ላይ መሆኗን ነው ብሏል መግለጫው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው ዓለማችንም ሆነች አሕጉራችን አፍሪካ አሁን ላይ የሚያስፈልጋቸው ፍጭትና ግጭት ሳይሆን የበለጠ ትብብርና ውይይት በመሆኑ ዛሬም በጋራ ለምናሸንፍባቸው መፍትሔዎች ኢትዮጵያ በሯ ክፍት ነው።